በአርብቶ አደሩ አከባቢ መጣል በጀመረው ዝናብ ለውጥ መኖሩ ተገለጸ

ሃምሌ 06፤2009

በአርብቶ አደር አካባቢ ዝናብ መጣል በመጀመሩ የተከሰተው የድርቅ ጫና እየቀነሰ መምጣቱን የፌዴራል አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በሚኒስቴር መስሩያ ቤቱ የአርብቶ አደር ክልሎችና አካባቢዎች ተመጣጣኝ ልማት ማረጋገጥ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሰውነት ቸኮል ለኢቢሲ እንደተናገሩት የዘነበው ዝናብ ለእንስሳቱ የውሃ እና ግጦሽ አቅርቦቱ የተሻለ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ቀደም ሲል በእንሳሰቱ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይከሰት ለምግብ ፍጆታ እና ወደ ሌላ አካባቢ የማሸሽ ሁኔታ ቢኖርም በአሁኑ ሰዓት ይህ ሁኔታ እየቀረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

ይህንንም ሁኔታ በአፋር ክልል ባደረጉት የስራ ጉብኝት ማረጋገጣቸውንና በክልሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጣለው ዝናብ የግጦሽ ሳር እያደገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

ወቅታዊ የሆኑ የድርቅ ችግሮችን የመከላከል ስራ ከመከናወኑም በተጨማሪ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት  ዘላቂ የልማት ስራዎች  ስራዎች መጀመራቸውን አቶ ሰውነት ገልጸዋል፡፡

እስካሁንም ከአንድ ሚሊዮን 800 ሺህ በላይ የሳር እስር ለአርብቶ አደሩ አካባቢ ማሰራጨት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ለዘላቂ መፍትሄው ከተከናወኑት ተግባራት መካከልም በኢትዮጵያ ሱማሌ፤ አፋርና ደቡብ ክልሎች 4 ሺህ 600 ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ በዘመናዊ መስኖ የመኖ ሳር ማልማት መቻሉንና በኦሮሚያ ክልልም ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ እቅድ መያዘዙን አብራርተዋል፡፡

በድርቤ መገርሳ