በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት ለሥራ ፈጠራ አነሳሽ እንዲሆን ተጠየቀ

ሐምሌ 04፣2009

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎችን የሥራ ፈጠራ ክህሎት ለማሳደግ በተቋማት የሚሰጠው የሥራ ፈጠራ ትምህርት አነሳሽ ሊሆን እንደሚገባ ተጠየቀ፡፡

በየዓመቱ ከከፍተኛ የመንግስት ትምህርት  ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች  ቁጥር እየጨመረ  መጥቷል ፡፡ በ2009  በአገሪቱ  ከሚገኙ  የመንግስት ትምህርት  ተቋማት ብቻ  126ሺ ተመራቂዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች  እና ደረጃዎች  ትምህርታቸውን   እንዳጠናቀቁ  ከትምህርት ከሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከዚሁ ውስጥ  109ሺ ተመራቂዎች  በመጀመሪያ ድግሪ  ትምህርታቸውን  የተከታተሉ ናቸው፣ቀሪዎቹ ደግሞ  በሁለተኛና ሶስተኛ ድግሪ ዘርፍ ተመራቂ ናቸው፡፡

የተመራቂዎች ቁጥርና  የአገሪቱ  የሰው ኃይል  የመቅጠር  አቅም  ባለመመጣጠኑ  ተመራቂዎች  ወደ ስራ ፈጠራ እንዲያተኩሩ ሲበረታቱም ይስተዋላል፡፡ ሆኖም  ከከፍተኛ ትምህርት የሚሰጠነው የስራ ፈጠራ ትምህርት በሚፈለገው ልክ  ለውጥ አለማምጣቱን ነው ለዘርፉ ቅርብ የሆኑ ባለሙያዎች ለኢቢሲ የገለፁት፡፡

ተመራቂዎች ያላቸውን ሰፊ ስራ የመፍጠርና  ውስን  የስራ ቅጥር አማራጮችን  በሚገባ  በማጤን  ፈተናዎቹን  ለመቋቋም  በመዘጋጀት ለደፊት ህይወታቸው  አዋጩን  መንገድ  ቢመርጡ መልካም መሆኑን ባለሙያዎቹ አመልክተዋል፡፡

በተለይም በአገር ውስጥ የሚገኙ  ስራ ፈጣሪዎች  ያለፉባቸውን   የፈተናና የስኬት ጉዞ  በትምህርት ስርዓቱ  በማካተት  ተማሪዎች  ከጅምሩ  ስራ የመፍጠር   ባህልና ዝንባሌያቸውን   ሊያሳድጉ እንደሚገባም ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል፡፡

የትምህርት ሚንስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠው ትምህርት ስራ ፈጠራ ክህሎትን በማዳበር ላይ መሰረት አድርጎ ለውጥ እንዲያመጣ እየተቃኘ  ነው ብለዋል፡፡

ለአብነት ያህል በሙያ፣ቴክኒክና ማሰልጠኛ ኮሌጆች የተግባር ትምህርት ድርሻ 70 በመቶ ፣ቀሪው 30 በመቶ ደግሞ የንድፈ ሀሳብ እንዲሆን መደረጉ ተመራቂዎችን ስራ ፈጣሪ ለማድረግ የታለመ ነው ብለዋል፡፡በዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ ጅምሮች ቢኖሩም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ለሚቀጥሉት 15 ዓመታት የሚያገለግል የስርዓተ ትምህርቱን ክፍተቶች የሚለይና የሚሞላ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ገልፃዋል፡፡

የትምህርት ተቋማት ከኢንዱስተሪዎች ጋር ተሳስረው እንዲሰሩ ማድረግና ሌች ጅመሮችም የስራ ፈጠራ ክህሎት ያለው የሰው ኃይለ ለማፍራት አይነተኛ ሚና እንደያሚበረክትም ሚንስትሩ ገልፀዋል፡፡

 

ሪፖርተር፤ እዮብ ሞገስ