በአፍሪካ በፍጥነት እየጨመረ ያለው የህዝብ ቁጥር አሳሳቢ መሆኑ ተጠቆመ

ከአለማችን ህዝብ ከ1 ቢሊዮን በላይ የሚሆነው ማለትም ካጠቃላዩ ህዝብ 13 በመቶው ከሳህራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የሚገኝ ነው፡፡

ይህ ቁጥር እኤአ 2050 በእጥፍ የሚጨምር ሲሆን በ2100 ደሞ ይህ ቁጥር 36 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ህዝብ ማለትም 4 ቢሊዮን የሚሆነው ከሳህራ በታች ባሉ አገራት ይሆናል፡፡

ከሳህራ በታች ባሉ አገራት የጨቅላ ህፃናት ሞት መቀነሱ በአንፃሩ ደግሞ ተመጣጣኝ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት አለመኖሩ ለህዝብ ቁጥር መጨመር እንደምክንያት ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት አንድ ከሳህራ በታች የምትገኝ እናት በአማካኝ 5 ልጆች ትወልዳለች፤ ይህ ቁጥር እኤአ 1970ዎቹ 6.7 ነበር፡፡

በቀጠናው ዘመናዊ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትም 26 በመቶ ብቻ በመሆኑ በዘርፉ በርካታ ስራዎች መሰራት እንዳለበት ያመለክታል፡፡

የህዝብ ብዛት መጨመር ከሰዎች ፍልሰት ጋር በተያያዘ ከአፍሪካ አልፎ ለአለም አገራት በተለይም ለአውሮፓ ከፍተኛ ስጋት ቢሆንም የዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱ መልካም ዜና ነው ተብሏል፡፡

በጀርመን ሀንቡርግ ከተማ በተካሄደው የቡድን 20 አገራት ባደረጉት ስብሰባ በአፍሪካ የተሻለ የስራ እድል ፈጠራ ጋር በተያያዘ ውይይት መደረጉ ለጉዳዩ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰጠውን ትኩረት ያመላክታል፡፡

የአህጉሪቱ መሪዎች የጤና አገልግሎትን ማሻሻል፣ ያለድሜ ጋብቻን በመከላከልና የሴቶች መብት ላይ ትኩረት በማድረግ ለጉዳዩ መፍትሄ ለመስጠት መንቀሳቀስ እንዳለባቸውን ነው የተገለፀው፡፡

ምንጭ፡- ፋይናንሻል ታይምስ