ቮልቮ ሁሉም ምርቶቹ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ለማድረግ ማቀዱን ገለጸ

ሰኔ 29፤2009

ቮልቮ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2019 ጀምሮ የሚያመርታቸው ሁሉም አውቶሞቢል ሞዴሎች በኤሌክትሪክ አሊያም በነዳጅና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መሆኑን ገለጸ።

ውሳኔው መሰረቱ በስዊድን ያደረገውና የቻይና ባለሀብቶች ንብረት የሆነው ኩባንያው በኤሌክትሪክ አሊያም በነዳጅና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አውቶሞቢሎችን የሚያመርት የመጀመሪያው የአለማችን ትልቁ መኪና አምራች ያደርገዋል ተብሏል።

በሁለት አይነት የሀይል ምንጭ የሚሰሩ መኪኖች በአለም ገበያ ያላቸው የሽያጭ መጠን አነስተኛ ቢሆንም ተቀባይነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ  ሃካን ሳሙኤልሰን ውሳኔው በነዳጅ መቀጣጠል ብቻ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ጊዜ እያበቃ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

በኤሌክትሪክ እና በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ዋጋቸው እየቀነሰ በመምጣቱና ቴክኖሎጂው በመሻሻሉ በብዛት እየተመረቱ መሆናቸው ተገልጿል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2010 ጀምሮ የእነዚህ ተሽከርካሪዎች ቁጥር እያደገ መጥቶ ባለፈው አመት ሁለት ሚሊዮን ተመርተዋል።

ቻይና አሜሪካን በመብለጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም ቀዳሚ መሆኗን ዘገባው አመልክቷል።