በአውሮፓ የሚበሩ አውሮፕላኖች የዋይፋይ ኢንተርኔት አገልግሎት ሊያገኙ ነው

ሰኔ 23፤2009

የእንግሊዝ ግዙፍ የሳተላይት ቴሌኮሚኒኬሽን ኩባንያ በአውሮፓ የአየር ክልል የሚበሩ አውሮፕላኖች የዋይፋይ ኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ወደ ጠፈር የሳተላይት መንኮራኩር ማምጠቁ ተነገረ፡፡

የአውሮፕላን ተሳፋሪ መንገደኞቹ የዋይፋይ የኢንተርኔት አገልግሎቱን የሚያገኙት ከአዲሱ ሳተላይት አልያም መሬት ላይ ካለ አጋዥ የኮምፒውተር መረብ እንደሆነ ቢቢሲ በዘገባው አስፍሯል፡፡ 

የሳተላይት መንኮራኩሩን ‹‹ጎዋና›› ከተባለ የፈንሳይ ግዛት እንዲመጥቅ ያደረገው ‹‹ኢንማርሳት›› የተሰኘ የእንግሊዝ ግዙፍ የሳተላይት ቴሌኮሚኒኬሽን ኩባንያ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ 

የኢንተርኔት አገልግሎቱ እ.ኤ.አ በ2017 መጨረሻ ላይ ሲጀመር የብሪታኒያ፣ ኤር ሊንጉሰ፣ አይቤሪያና ቮሊንግኤ የተባሉ የአየር መንገዶች ቀዳሚ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡

 

አየር መንገዶቹ የዋይፋ አገልግሎቱን ለማግኘት አውሮፕላኖቻቸው ላይ አንቴናን ጨምሮ አስፈላጊ መሳሪያዎች እንደሚተክሉ ተመልክቷል፡፡  

የአየር መንገደኞቹ ምድር ላይ ሆነው በተለያዮ ስፍራዎች ኢንተርኔት እንደሚጠቀሙ ሁሉ በአውሮፕላን ጉዟው ወቅት ተመሳሳይ አገልግሎት እንደሚያገኙ ዘገባው ጠቁሟል፡፡