የህጻናት የልብ ሕክምናን ለማጠናከር የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ

ሰኔ 21፤2009

የህጻናት የልብ ሕክምናን ለማጠናከር ከተለያዩ አካላት ጋር የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል  ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ

ጠቅላይ ሚንስትሩ በልብ ሕክምና ሙያ የተሰማሩ ከእስራኤል የመጡ ልኡካን ቡድኖችን ተቀብለው አነጋግረዋል።

ለሰላሳ የልብ ህሙማን ህጻናት ቀዶ ጥገና ለማድረግ ለአንድ ሳምንት የመጣው የሀኪሞች ልኡክ ጥቁር አንበሳ በሚገኘው የልብ ህሙማን የህጻናት መርጃ ማእከል ለአስራ ሶስት ህጻናት ቀዶ ጥገና አከናውኗል።

ወደፊትም የሕክምና ትምርታቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው የሚመለሱ የልብ ሀኪሞች በቀዶ ሕክምናው ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ባለፈ ለሌሎች የሕክምና ባለሞያዎች የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደሚያስችል ቀዶ ሕክምናውን ከሚያከናውኑ ሀኪሞች አንዱ የሆነው ዶክተር ያየህይራድ መኮንን ተናግሯል።

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የህጻናት የልብ ህመም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ገልጸው  መንግስት ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑ መናገራቸውን የጠቅላይ ሚንስትሩ  ቃል አቀባይ አቶ እውነቱ ብላታ  ተናግረዋል።

መንግስት ይህንን ጅምር ለማጠናከር  መዘጋጀቱንም ጠቅላይ ሚንስትሩ  ተናግረዋል።

የሀኪሞቹ ቡዱን ከዚህ በፊት በእስራኤል ለ600 ኢትዮጵያውያን ህጻናት የልብ ቀዶ ሕክምና አከናውኖ  ወደ አገራቸው መመለሱ ተገልጿል።

ሪፖርተር:-ፋሲካ አያሌው