ቴክኖሎጂ የአፍሪካን ሁለንተናዊ የጤና እንክብካቤ ለማሳደግ የጎላ ድርሻ አለው

ሰኔ 20፤2009

በአፍሪካ ዘመናዊ የጤና  አጠባበቅ  ዘዴን በማስፋፋትና ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከማድረስ ረገድ የቴክኖሎጂ ቅንጅት ትልቅ ድርሻ እንዳለው የአለም ጤና ድርጅት ገለጸ፡፡

በአፍሪካ የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ማትሺዲሶ ሬቤካ ሞኤቲ በዚህ ሳምንት በሩዋንዳ የሚካሄደውን የመጀመሪያው የአለም ጤና ድርጅት  የአፍሪካ የጤና ፎረም  አስመልክተው  እንደተናገሩት ብዙ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም  የቀጠናውን የጤና እንክብካቤ ለማዳረስ ትልቅ ድርሻ አለው፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ ቴክኖሎጂ መረጃ ለማስተዳደር፣ ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና ለመስጠት ፣ የሪፈራል ስራዎችንና ሌሎችንም ለመስራት ያግዛል፡፡

በሩዋንዳ ኪጋሊ የሚካሄደው ስብሰባ  በመንግስታት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጀንሲዎች፣ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና በአፍሪካ በሚገኙ የግል ዘርፍ ቅንጅታዊ አሰራር አጠቃላይ የጤና ተደራሽነትን ለማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይመክራል፡፡

 ምንጭ -ሮይተርስ