ለክረምት የወጣቶች በጎ አድራጎት ተግባር በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረግ አለበት

ሰኔ 12-2009

ዘንድሮ የሚካሄደው የክረምት የወጣቶች በጎ አድራጎት ተግባር በሚፈለገው መጠን አገሪቱ ተጠቃሚ  እንድትሆን ለወጣቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠርና በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

ኢትዮጵያ በ2002 ዓ.ም. የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን በተቀናጀ አግባብ በመምራት ብዛት ያላቸው ወጣቶች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ እንዲሰማሩ የሚያስችል የበጎ ፍቃድ ደረጃ በ2002 አውጥታለች፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ  ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያም  ዘንድሮ በሚካሄደው  የበጎ አድራጎት ስራ  አገሪቱ ተጠቃሚ እንድትሆን  በቅድመ ዝግጅት ላይ ትኩረት መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡

የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች  የበጎ አድራጎት ስራው ግቡን ይመታ ዘንድ የቅንጅት ስራው  ላይ መስራት አለብን ብለዋል፡፡

በክረምት ወራት ብቻ ስኬታማ የሆነውን ዘርፉን በበጋ ወራትም ማስቀጠል እንዳለበት አክለው  ገልጸዋል፡፡

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳ መድረኩ የዩኒቨርሲቲና ከዩኒቨርሲቲ ውጪ  ያሉ ወጣቶች የሚሰማሩበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር የእቅድ ዝግጅት ለማድረግ አላማ መያዙን ገልጸዋል፡፡

ተግባሩ በተቀናጀ መልኩ  እንዲሰራና ባህል እንዲሆንም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ  በፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ  መንግስት በበኩሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለበትና  አሁንም ዝግጅት  እየተደረገ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡  

ዘንድሮ በመላው አገሪቱ ከ8 በላይ በሚሆኑ መስኮች 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶች በበጎ አድራጎት ተግባሩ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡