የሚንስትሮች ምክር ቤት በ2 ስምምነቶችና ሶስት አዋጆች ላይ ውሳኔ አስተላለፈ

ሰኔ 9፤2009

የሚንስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 32ኛው መደበኛ ስብሰባ ሁለት ስምምነቶችንና ሶስት አዋጆች ላይ ውሳኔ አስተላለፈ።

ከስምመነቶቹ አንዱ ፖሊ.ጂስ.ኤል ፔትሮሌም ኢንቨስትመንት ሊምትድ የተባለውና በብሪቲሽ ቨርጂን አየርላንድስ የተመሰረተ ኩባንያ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኦጋዴን አከባቢ ካሌብ እና ሂላላ የሚሰኙ የጋዝ ልማት ስፍራዎች ቀደም ሲል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ጂቡቲ ወደብ ለማጓጓዝ የሚያስችል ቧንቧ ከኦጋዴን እስከ ጅቡቲ ወደብ ለመዘርጋት መብት የሚሰጠው ነው።

ዋይ.ኤም.ጂ ኃላፊነቱ  የተወሰነ የገል ማሕበር በአነስተኛ ደረጃ የጽንሰ ወርቅ ማዕድን ማምረት ኢንቨስትመንት ከማስፋፋት ጋር ፋይዳው ትልቅ መሆኑ የሰጠው ፍቃድ ሌላኛው ምክር ቤቱ ውሳኔ የሰጠበት ነው።

ምክር ቤቱ የኤሌክትሮኒክ ፊርማን ለመደንገግ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይም መክሯል።

በአገሪቱ ኤሌክትሮንክ ንግድና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዙ  የመንግስት አገልግሎቶችን ለማበረታታት ምቹ የሕግ ማዕቀፍ መፍጠር፣ የኤሌክትሮኒክ መልእክት ልውውጥን በተመለከተ ሕጋዊ ዕውቅና መስጠትና የተሳታፊዎችን መብትና ግዴታ በግልጽ መደንገግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ላይ ተወያይቷል።

እንዲሁም በኤሌክትሮኒክ መልዕክት ልውውጥ ወቅት የተሳታፊዎችን ማነትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መተማመን ለመፍጠር የሚያስችል ሕግ ማውጣት በማስፈለጉ ምክር ቤቱ አዋጁ ላይ በመምከር እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗ።

ምክር ቤቱ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና ብሔራዊ መታወቂያ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ላይም ተወያይቷል።

የሚንስትሮች ምክር ቤት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ከተጀመረ በሃላ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ የአሰራር ክፍተቶን ለመቅረፍ ብሎም አገልግሎቱን የተሟላ ለማድረግ የወሳኝኩነት እና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 760/2004ን በማሻሻል እንዲጸድቅ ለሀዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።

ምክር ቤቱ ስለ ዕጸዋት አጽዳቂ መብት የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይም ተወያይቶ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።