በስኳር ፋብሪካዎች ግንባታና በአገዳ ልማት መካከል የሚስተዋለውን ያለመጣጥጣም ችግር እንድፈታ ተጠየቀ

ሰኔ 9፤2009

የስኳር ኮርፖሬሽን በስኳር ፋብሪካዎች ግንባታና በአገዳ ልማት መካከል የሚስተዋለውን ያለመጣጥጣም ችግር ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባው የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

 ቋሚ ኮሚቴ የስኳር ኮርፖሬሽን የ 2009 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል።

የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታን በተመለከተ የኦሞ ኩራዝ አንድና ሁለት በቅደም ተከተል 93 እና 94 በመቶ  የደረሱ ሲሆን የኦሞ ኩራዝ ሁለት ስኳር ፋብሪካ ማምረት መጀመሩን የኮርፖሬሽኑ የስራ ኃላፊዎች ገልጸዋል።

የኦሞ ኩራዝ ሶስት ግንባታ የተጠናቀቀ ሲሆን ግንባታው በዚህ ዓመት የተጀመረው ኦሞ ኩራዝ አምስት የመጀመሪያ ግንባታ ስራዎች ጥሩ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ ኃላፊዎቹ አስረድተዋል።

የጣና በለስ አንድ እና ሁለት የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ  77 እና  25 በመቶ እንዲሁም በዚህ ዓመት ወደ ግንባታ የገባው የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ ስራው ከግማሽ በላይ መከናወኑንም ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ የሰው ሀይሉን ለማሟላትና አቅም ለመገንባት መስራቱን ቋሚ ኮሚቴው በተሻለ አፈጻጸም ገምግሟል።

የካይዘን ለውጥ አመራር በፋብሪካዎች መተግበሩን እንዲሁም ዘርፉን በጥናትና ምርምር ለመደገፍ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር መፍጠሩን በበጎ ጎን አንስቷል።

ቋሚ ኮሚቴው በውጤት የሚለካ  ኪራይ ሰብሳቢነትን የመከላከል ስራ  እንዲሁም ስኳር በበቂ መጠን ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከማምረት ባለፈ ወደ ውጭ ለመላክ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ  አሳስቧል።

ኮርፖሬሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ  አሰራር ይበልጥ ሊያጠናክር እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል።

ሪፖርተር:-ተሾመ ወልዴ