የመንግስታቱ ድርጅት አዲስ የፀረ ሽብር ቢሮ ሊያቋቁም ነው

ሰኔ9፤2009

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ አገራት ሽብርተኝነትን አስቀድመው ለመዋጋት የሚያስችሏቸውን እስትራቴጂ ለመንደፍ ያስችላል ያሉትን አዲስ የፀረ ሽብር ቢሮ ለማቋቋም ወስኗል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የፖለቲካ ጉዳዮች (DPA) ስር የነበሩ አንዳንድ ተግባራትንም ወደ አዲሱ የፀረ ሽብር ቢሮ ለማሸጋገርም ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በዚህ መሰረት ቀድሞ በፖለቲካ ጉዳዮች (DPA) ስር የነበሩት የፀረ ሽብር ግብረ ሀይል ቢሮ (CTITF) እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የፀረ ሽብር ማእከል ወደ አዲሱ ቢሮ እንዲዘዋወሩ ይደረጋል፡፡

አዲስ የሚቋቋመው ቢሮም በዋና ፀሀፊው ስር እንዲተዳደር እንደሚደረግም የተባበሩት መንግስታት አስታውቋል፡፡

አዲሱ ቢሮ 5 ዋና ዋና ተግባራትን ለማስፈፀም የተቋቋመ ሲሆን ተግባራቱም በጠቅላላ ጉባኤ የተሰጠውን የፀረ ሽብር ጉዳዮች በሃላፊነት መምራት፣ ሽብርን ለመከላከል በስሩ የተቋቋሙ አራት በፀረ ሽብር ስር የሚገኙ መሰረቶችን ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ለአባል አገራት የአቅም ግንባታ መስጠት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ሽብርን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት መደገፍና ቅድሚያ እንዲሰጠው ማስደረግ ናቸው፡፡

ምንጭ፡- የተባበሩት መንግስታት