ግዙፉ ጄነራል ኤሌክትሪክ ኩባንያ ቢሮውን በአዲስ አበባ ከፈተ

ግንቦት 11፣2009

በዓለም ግዙፉ የዲጂታል ኢንዱስትሪ ኩባንያ የሆነው ጄነራል ኤሌክትሪክ በአዲስ አበባ ቢሮውን ከፈተ።

በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ በአፍሪካ የኩባንያው ፕሬዝዳንትና ስራ አስፈጻሚ ጃይ አየርላንድ እና በኢትዮጵያ የጄኔራል ኤሌክትሪክ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዳንኤል ሃይሉና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ እንዳሉት የጄነራል ኤሌክትሪክ በኢትዮጵያ ቢሮውን መክፈቱ መንግስት ምቹ የቢዝነስ አካባቢን ለመፍጠርና የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ የሚያደርገው ጥረት አንዱ ማሳያ ነው።

ይህም ጥረት መንግስት ሀገሪቱ በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ የያዘችው አገራዊ ግብ አካል ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የጀኔራል ኤሌክትሪክ ስራ አስፈጻሚው አቶ ዳንኤል ሃይሉ ኩባንያው በኢትዮጵያ ስራውን ከጀመረ ዘጠኝ ዓመታት ያስቆጠረ መሆኑን ገልፀው፤ የሰው ሃይሉን በማጠናከር ሀገሪቱ በሃይል፣ በትራንስፖርት እና በጤናው መስክ ስኬት ለማስመዝገብ በምትሰራው ስራ የበኩላችንን ለማበርከት እንሰራለን ብለዋል።

በኢትዮጵያ አዲስ በተከፈተው ቢሮው አማካኝነትም በሀገሪቱ ካሉ የግል ዘርፎች እና ኢንተርፕራይዞች ጋር በመቀናጀት የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ስራን ያከናውናል ነው የተባለው።

ኩባንያው ለሀገሪቱ ሁለተኛ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ስኬት አስተዋጽኦ በማድረግ የኢንዱስትሪ እድገትን እንደሚያፋጥንም ተገልጿል፡፡

ጄነራል ኤሌክትሪክ የአፍርካ የኢንቨስትመንት አጋርነቱን ለማጠናከር በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉ 33 ሀገራት 2 ሺህ 600 ሰራተኞችን ይዞ እየሰራ ነው።

በዚህም እንቅስቃሴው ኩባንያው በ2016 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ አግኝቷል።

ምንጭ፦ ጄነራል ኤሌክትሪክ ኩባንያ