በኬንያ ናይሮቢ ኮሌራ መከሰቱ ተዘገበ

ግንቦት 11፣2009

በኬንያ ናይሮቢ 5 ሰዎች በኮሌራ መያዛቸው ተረጋገጠ፡፡

በዋና ከተማዋ ከረን በተባለ አካባቢ አምስት ሰዎች በኮሌራ በሽታ መያዛቸውን ተከትሎ ወደ ወረርሽኝ እንዳያድግ  ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ናይሮቢ አሳስባለች፡፡፡

የናይሮቢ ቀጠና የጤና ኃላፊ  የሆኑት  በርናርድ ሙያ በሽታው  በአምስት ሰዎች ላይ መገኘቱን አረጋግጠዋል፡፡ በሽታው ይከሰት እንጂ  እስካሁን የሞተ ግለሰብ  አለመኖሩን አረጋግጠዋል፡፡

ከናይሮቢ ቀጠና ውጭ በሽታው በሌሎች ሁለት ቀጠናዎች ማለትም በጋሪሳና ሙራንግ መከሰቱም ተመልከቷል፡፡

ክትትል እየተደረገላቸው ከሚገኙ ሶስቱ በካረን በሰርግ ላይ የነበሩ በመሆናቸው በሽታው ከምዕራባዊ ኬንያ ተነስቶ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡

የበሽታውን ስርጭት ለመግታትና ሁኔታውን ለመከታተል  የህክምና  ማእከላት  ተቋቁመዋል ተብሏል፡፡

በኬንያ  የኮሌራ በሽታ ለመጨረሻ ጊዜ የታየው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 ነበር፡፡

በሽታው በአብዛኛው በባክቴሪያ፣ በተበከለ ምግብና ውሃ አማካኝነት የሚከሰት ሲሆን በባክቴሪያው ከተያዘ ሰው በሰገራ አማካኝነት በቀላሉ በንክኪ ይተላለፋል፡፡

የኮሌራ  በሽታ ህክምና ካላገኘ  ተቅማጥ በማስያዝ ከድርቀት እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል፡፡

በአለማችን በየአመቱ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ህዝብ በኮሌራ በሽታ እንደሚያዝና ከ21 ሺህ እስከ 143 ሺህ ደግሞ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

ምንጭ  ፡‑ ሲጂቲኤን