የኳታሩ ኤዝዳን በአዲስ አበባ መዋለንዋይ ሊያፈስ ነው

ግንቦት 10፣ 2009

የኳታሩ ኤዝዳን በአዲስ አበባ ባለ ብዙ ዘርፍ ሪል ስቴት መገንባት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ስምምነቱን ከንቲባ ድሪባ ኩማ እና የኢዝዳ ግሩብ ተወካይ ያደረጉ ሲሆን ሰፊ የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል፡፡

ፕሮጀክቱ በ60 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ ሲሆን ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል፣ የስብሰባ ማዕከል፣ ባለ ማማ አፓርትመንትና ቢሮዎች፣ የተለያዩ ሱቆችና ዘመናዊ ሬስቶራንትና ካፌዎች ይኖሩታል ተብሏል፡፡

ስምምነቱ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኤዝዳን ግሩብ  በኢትዮጵያ የሚያከናውነው ኢንቨስትመንት አዋጭ እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

አዲሱ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ያለውን የቱሪስት ፍስት እንደሚጨምርም በስምምነቱ ዕምነት ተጥሎበታል፡፡

የኤዝዳን ቢዝነስ ግሩፕ ሃላፊ ዶ/ር ካሊድ ቢን ታኒ በመስከረም ወር አዲስ አበባ ይጎበኛሉ፡፡ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ አንደሚነጋገሩ ተገልጿል፡፡

ኩባንያው በኳታር የገነባውን ዘመናዊ ሪል እስቴት በልዑካን ቡድኑ መጎብኘቱን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

ምንጭ፡- መርከብ ረዳ