ጉዳት የደረሰበት የአዳማ አሰላ መንገድ ጊዜያዊ ተለዋጭ መንገድ ተበጀለት

ግንቦት 9፣ 2009

ባለፈው ቅዳሜ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተፈጠረው ጎርፍ ዶዶታ አካባቢ ጉዳት ለደረሰበት የአዳማ አሰላ መንገድ ጊዜያዊ አማራጭ መንገድ ተከፈተ፡፡

የአርሲ ዞን መንገዶች ባለስልጣን ሃላፊ አቶ ከድር ሁሴን እንደገለጹት በመሬት መንሸራተቱ ምክንያት 9 ኪሎ ሜትር የሚሆን መንገድ ላይ ጉዳት በመድረሱ ነው ጊዚያዊ ተለዋጭ መንገድ ለመክፈት አስገዳጅ የሆነው፡፡

የአማራጭ መንገዱ መከፈት  የትራፊክ ፍሰቱ መስተጓጎል እንዳይፈጠር ለማድረግ  መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት  የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ኃላፊነት መሆኑን የአርሲ ዞን መንገዶች ባለስልጣን ሃላፊ አቶ ከድር ሁሴን ገልፀዋል፡፡

ችግሩ በተፈጠረበት አካባቢ ቅርብ ርቀት ላይ የሚኖሩና ስጋት ያለባቸው ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ነዋሪዎቹን ወደ ሌላ ቦታ የማዘዋወር ስራ እየተሰራ መሆኑን ተመልክቷል ፡፡

የአፈሩ ባህሪ በቀላሉ የሚሸረሸር በመሆኑና ግንባታው ሲከናወን ወደ መንገዱ ውሃ ሲገባ የሚስተናገድበት ቦይ ባለመኖሩ ችግሩ መፈጠሩን ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

ይህ ጉዳት እንደሚደርስ ተገምቶ ባለፈው አመት በተሰራ ስራ መጠነኛ መሻሻል ቢታይም አሰራሩ አጥጋቢ ባለመሆኑ ነው ችግሩ የተፈጠረው፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የተደረመሰውን መንገድ በአስቸኳይ ለመጠገን እየተንቀሳቀሰ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የባለስልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለኢቢሲ እንደገለፁት ላጋጠመው ችግር አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የጥገና ቡድን ወደ ስፍራው አምርቷል።

ችግሩንም ዘላቂ በመሆነ መንገድ ለመፍታት ተጨማሪ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡

የአዳማ አሰላ መንገድ 75 ኪሎ ሜትሮች የሚረዝም ሲሆን ለ8 ዓመታት አገልግሏል፡፡

ሪፖርተር፡- እዮብ ሞገስ