ኢቢሲ እና አልጀዚራ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

ግንቦት 9፣ 2009

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮፖሬሽን (EBC) እና አልጃዚራ ሚዲያ ኔትዎርክ በስልጠናና ልምድ ልውውጥ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ::

አልጀዚራ ሚድያ ኔትዎርክ በአጭር ጊዜ በአለም ላይ ተፅእኖ መፍጠር የቻለ ሚድያ በመሆኑ ተቋሙ ያለውን የባለሞያዎች፣ የቴክኖሎጂና የአሰራር ልምድ ለመቅሰም በሚል ተመራጭ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ስምምነቱን የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ስዩም መኮንን እና የአልጃዚራ ሚዲያ ኔትዎርክ የስልጠና ማእከል ዋና ዳይሪክተር ሞኒር ዳይሚ መካከል ተፈርሟል፡፡

ኢቢሲ ከአልጀዚራ ዘርፈ ብዙ ልምድ ከፍተኛ ልምድ ሊቀስም እንደሚችልና ጉብኝቱ ተቋሙ የጀመረውን የለውጥ ሂደት እንደሚያግዝ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ገልፀዋል፡፡

የአልጀዚራ ባለሞያዎች ከአንድ ወር በኋላ በኢቢሲ ጉብኝት በማድረግ ያሉበትን ክፍተቶች እንደሚለዩና ድጋፍ የሚያርጉባቸውነ  ጉዳዮች እንደሚለዩም ተናግረዋል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ስዩም መኮንን እና በኳታር የኢፌድሪ ኤምባሲ ልዩ መልዕክተኛና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በተገኙበት የአልጀዚራ ልዩ ልዩ የስራ ክፍሎች ጉብኝት የተደረገ ሲሆን የመግባቢያ ሰነዱን ወደ ተጨባጭ ውጤት ማሸጋገር በሚቻልባቸውና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሄዷል::

ሪፖርተር፡- መርከብ ረዳ  (ከዶሀ)