አንድ ጥንድ የጆሮ ጌጥ ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ ተሸጠ

ግንቦት 9፣ 2009

አንድ ጥንድ ከአልማዝ የተሰራ የጆሮ ጌጥ ከ57 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተሸጠ፡፡

አፖሎ እና አርቴሚስ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ጥንዶቹ የአልማዝ ጆሮ ጌጦች በሮዝና ሰማያዊ ቀለማት የቀረቡ ናቸው፡፡

እያንዳንዳቸው ተመሳሳይ ቅርፅ ያላቸው 16 ካራት የሆኑ የአልማዝ ጆሮ ጌጦቹ በዚህ ውድ ዋጋ ሲሸጡ የአለም ክብረ ወሰንን እንዲጨብጡ አድርጓቸዋል፡፡

አፖሎ የተሰኘው ሰማያዊው ጆሮ ጌጥ በተናጠል 42.5 ሚሊዮን ዶላር ሲያወጣ አርቴሚ የተሰኘው ባለ ሮዝ ቀለም ጆሮጌጥ ደግሞ 15.5 ሚሊዮን ዶላር ነው የተሸጡት፡፡

የአልማዝ ጆሮጌጦቹ በውድነታቸው የአለም ሪከርድን ለመስበር ቢችሉም ይሸጣሉ ተብለው የተሰጣቸውን 70 ሚሊዮን ዶላር የዋጋ ግምት ግብን ሳያሳኩ ቀርተዋል፡፡

ምንጫቸው ከደቡብ አፍሪካ የማእድን ስፍራ እንደሆነ የተገለፀው የአልማዝ ጆሮ ጌጦች እጅግ ውድና ብርቅዬ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

ጥንዱን የጆሮ ጌጥ የገዛው አንድ ግለሰብ ሲሆን ማንነቱ ይፋ አልተደረገም፡፡ 

ምንጭ፡- ቢቢሲ