“አብቁተ” ለአለም አቀፍ የፋይናንስ ሽልማት ዕጩ ሆኖ ተመረጠ

ግንቦት 8፣ 2009

የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም "አብቁተ" የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነት በሚል ዘርፍ ለአለማቀፍ የፋይናንስ ሽልማት ዕጩ ሆነ፡፡

በአገሪቱ ከሚገኙ 35 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በመላው አማራ ክልል የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋፋት በመንቀሳቀሱ ነው "ፋይናንሻል ኢንክሉዥን" ሽልማት እጩነት ያበቃው፡፡

የፋይናንስ ተቋሙ እያንዳንዱን ሰው የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ብቻም ሳይሆን በፋይናንስ ስርአቱ ውስጥ ተገቢ የሆነ ተጠቃሚነት እንዲኖረውም ከፍተኛ ሚና መጫወቱን የአብቁተ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መኮንን የለውምወሰን ገልፀዋል፡፡

በአገሪቱ ዘመናዊ የኢንተርኔትና የሞባይል መሰረተ ልማት አገልግሎቶች ውስን መሆናቸው በፋይናንስ ተደራሽነቱ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንደሚያሳድር ይታመናል፡፡ 

በዚህም ረገድ አብቁተ ባለፉት 2 ዓመታት ህብረተሰቡን ለመድረስ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ዝርጋታ የማስፋፋት ስራ በከፍተኛ ደረጃ ማድረጉን አቶ መኮንን የለውምወሰን በተለይ ለኢቢሲ ገልፀዋል፡፡

የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በ500 የቅርጫፍ ጽህፈት ቤቶችና ከ1 ሺህ 200 በላይ በሚሆኑ ሳተላይት ጽህፈት ቤቶች የፋይናንስ አገልግሎት በተለይም በገጠር ለሚኖረው ማህበረሰብ በማቅረብ ላይ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

ከ12 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሰማራው አብቁተ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ቁጥር ላለው ማህበረሰብ በቁጠባ፣ በብድር፣ በኤሌክትሮኒክ ክፍያና ገንዘብ መላላክ በኩል ያሉትን አገልግሎቶች በሙሉ በመስጠት ላይ እንደሚገኝም ነው አቶ መኮንን የገለፁት፡፡

በገጠር የሚካሄዱ የፕሮጀክት እንቅስቃሴዎችና አርሶአደሩ የሚያደርጋቸውን ማንኛውንም ክፍያዎች በሙሉ በአብቁተ በኩል እንዲያደርግ ከፍተኛ የማስተሳሰር ስራ መሰራቱም ለስኬቱ ምንጭ መሆኑ ተገልጿል፡፡

አብቁተ በተለይ የገጠሩን የግብዓት ስርጭትና የብድር ስርአት መቶ በመቶ ሽፋን በመስጠት ላይ የምገኝ ተቋም ሲሆን በየአመቱ ከ4 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ የማዳበሪያ ስርጭትንም ያስተዳድራል፡፡

ተቋሙ በመደበኛነት የሚካሄደው የብድር ስርጭት ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን ከ6 ሚሊዮን በላይ የከተማና የገጠር ነዋሪዎችም የተቋሙ የቁጠባ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡

አብቁተ "ኤም ብር" በተሰኘው የሞባይል ቴክኖሎጂ በመጠቀም በየወሩ እስከ 1 ቢሊዮን ብር እንደሚያንቀሳቀስ የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው የነዚህ ውጤታማ ስራዎች ድምር ተቋሙን በተደጋጋሚ ለሽልማት እንዳበቃው ገልፀዋል፡፡  

"አፍሪካ ባንከር አዋርድ" የሚባለውና በየዓመቱ በሚያካሂደው በፋይናንስ ዘርፍ ላይ ያተኮረ ውድድር ለሽልማት የታጨው የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ከዚህ ቀደምም በዚሁ ድርጅት የዓመቱ ምርጥ የብድርና ቁጠባ ተቋም ተብሎ መሸለሙን አቶ መኮንን ገልጸዋል፡፡ 

በናትናኤል ፀጋዬ