ብራዚል በዚካ ቫይረስ ምክንያት ያወጀችውን ብሄራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ አንስታለች

ግንቦት 5፣ 2009

የዚካ ቫይረስ ስርጭት መቀነሱን ተከትሎ ብራዚል አውጃ ቆየችውን ብሄራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ አንስታለች፡፡

ባለፉት ሶስት ወራት በሽታው ከዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ95 በመቶ በመቀነሱ ነው አዋጁ እንዲነሳ የተደረገው፡፡

የዚካ ቫይረስ ህጻናት አነስተኛ የራስ ቅል እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሲሆን ብራዚል የሪዮ ኦሎምፒክን ልታዘጋጅ በተቃረበችበት ወቅት ነበር የተከሰተው፡፡

ብራዚል ከአንድ ዓመት በፊት ከ170 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውን ተከትሎ ነበር የአደጋ ጊዜ አዋጅ ያወጀችው፡፡

ከዚህ በኋላም የቫይረሱ ስርጭት ተስፋፍቶ በቫይረሱ የተጠቁ ህጻናት በ30 አገራት መወለዳቸው ይታወሳል፡፡

ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያወጀውን የአደጋ ጊዜ አዋጅ ከወራት በፊት ማንሳቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡