የቱሪስቶችን ቁጥር አንድ ሚሊዮን ለማድረስ እየተሰራ ነው-ሚኒስቴሩ

ግንቦት 4፣2009

በበጀት አመቱ በአገሪቱ የተለያዩ ታሪካዊና ሀይማኖታዊ ተቋማትን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር እስከ አንድ ሚሊዮን ለማድረስ መታቀዱ ተገለጸ፡፡

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብና አለም አቀፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛሃኝ አባተ ለኢቢሲ እንደገለጹት መስሪያ ቤቱ በበጀት አመቱ አገሪቱ ከሚጉበኙ አንድ ሚሊዮን ቱሪስቶች 3 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል፡፡

በመጀመሪያውና በሁለተኛው ሩብ አመት በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የቱሪስት ቁጥር መቀነስ ተይቶ እንደነበረና በአሁን ሰአት ግን የጎብኚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አቶ ገዛሃኝ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት 439 ሺህ 359 የውጭ አገር ቱሪስቶች አገሪቱን መጎብኘታቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር 8 ነጥብ 25 በመቶ ቅናሽ ታይቷል ብለዋል ፡፡

በላፉት ስድስት ወራት አገሪቱን ከጎበኙ ቱሪስቶችም 1.6 ቢሊዮን አሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንና የገቢ መጠንም ከ2008 ዓ.ም የ6 ወራት አንጻር 148 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ቅናሽ ማሳየቱ ታውቋል፡፡

በየአመቱ አገሪቱን የሚጎበኙ ቱሪስቶች ቁጥር ከ10 በመቶ በላይ እያደገ መምጣቱንም አቶ ገዛሃኝ ተናግረዋል፡፡

የቱሪዝም ፍሰቱን የበለጠ ለማሳደግ አዳዲስ የመዳረሻ ቦታችን  የማልማት ፤ነባሮችን ወደ  ተሻለ ደረጃ የማድረስ እንዲሁም በገጽታ ግንባታው አገሪቱን በስፋት የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን መጨረሻም ከ2 ሚሊዮን ባላይ ቱሪስቶች አገሪቱ እንዲጎበኙ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ገዛሃኝ በዚህም ረገድ ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ፣ በዋጋ ተመጣጣኝ፣ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ፣ ቱሪስቱን ሊጋብዙ የሚችሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየተስፋፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በድርቤ መገርሳ