አፍሪካ ዘመናዊ ግብርናን ለመፍጠር የሚያግዝ የዘለቂ የግብርና ሜካናይዜሽን ስትራቴጂ ይፋ አደረገች

ግንቦት 4፣2009

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ዘመናዊ ግብርናን ለመፍጠር የሚያግዝ የዘለቂ የግብርና ሜካናይዜሽን ስትራቴጂ ይፋ አደረገ።

ስትራቴጂው የሕብረቱ አባል አገራት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 የተሰማሙበትን በ2025 አፍሪካን ከረሀብ ነጻ የማድረግ እቅድ ለማሳካት ያለመ ነው ተብሏል።

የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2025 አህጉሪቱን ከረሀብ ነጻ ለማድረግ የማላቦ ስምምነት በ2014 አጽድቀዋል።

በስምምነቱ የአህጉሪቱን የግብርና ምርት በዕጥፍ ለማሳደግ ታቅዷል።

ይህን ሰፊና የአጭር ጊዜ እቅድ ለማሳካት ብሎም በ2030 ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ለሚገመተው የህዝብ ቁጥር መቀለብ የሚችል አቅም ለመፍጠር ግብርናን ሜካናይዝድ ማድረግ ቀዳሚ አጀንዳው ነው።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብና ግብርና ተቋም /ፋኦ/ በመተባበር ቀጣይነት ያለው የግብርና ሜካነይዜሽን ስትራቴጂ አዘጋጅቷል።

የስትራቴጂ ረቂቅ ሰነዱ  ዘመናዊ  ግብርናን መፍጠር፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችንና ማሽነሪዎችን ተደራሽ ማድረግ፣ በምርት አሰባሰብ የሚታዩ ብክነቶችን ማስወገድ እንዲሁም ገበያ ተኮር የአየር ንብረት ለውጥን የሚቃቃም ምርት ማምረት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

ሰነዱ ወጣቶች ወደ ግብርና የሚገቡበት፣ የሴቶች አቅም የሚጠናከርበት፣ የግል ዘርፉ ለዘላቂ የግብርና ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርግበት አቅጣጫዎችም አስቀምጧል።

አህጉሪቱ በዘርፉ ያላትን ሰፊ ዕድል ልትጠቀምበት ይገባልም ተብሏል። አባል አገራቱም የግብርና ፖሊሲያቸው አካል ያደርጉታል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ስትራቴጂም ሆነ ሌሎች ዕቅዶች ውጤታማ እንዲሆኑ ግን በአህጉሪቱ ሰላምና መረጋጋት ሊኖር ይገባል ተብሏል።

የሜካናይዜሽን ጥረት ተግባራዊ ለማድረግ የምርምር ማዕከላትና ዩኒቨርሲቲዎች ቴክኖሎጂዎችን በማላመድ፣ አርሶ አደሩ በማሰልጠን፣ የግብርና ቴክኖሎጂ ጥገናና በአገር ውስጥ የማምረት አቅም ለማሳደግ ሚናቸው የጎላ ነው ተብሏል። ሰነዱ ባለድርሻ አካላት እየመከሩበት ይገኛሉ።

ሪፖርተር:-ሙሉጌታ ተስፋይ