ኢትዮጰያና ሲንጋፖር ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

ግንቦት 4፣2009

ኢትዮጵያና ሲንጋፖር ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውን ገለጹ፡፡

የሲንጋፖሩ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ቴዮ ቺ ሄየን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተወያይተዋል።

የሲንጋፖር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ  ከምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጣይ ወር ከአዲስ አበባ ሲንጋፖር ዳግም የሚጀመረው  ቀጥተኛ በረራ  በሁለቱ አገራት ያለው የህዝብ ለህዝብና  የንግድ ግንኙነቱ እንደሚያጠናክረው መግለጻቸው አመልክቷል።

በሁለቱ አገራት የተጀመሩ የሁለትዮሽ ድርድሮች በማስቀጠል ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሹ መግለፃቸውንም ዘገባው አመልክቷል።

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሲንጋፖር ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፕሮግራም ላይ እንዲሳተፉ መጋበዛቸውንና የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚንስትር ሊ ሀይሰን ሉንግስ አገራቸውን እንዲጎበኙ ያደረጉላቸውን ጥሪ መቀበላቸውንም የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ በቆይታቸው በኢትዮጵያ ከተሰማሩ የሲንጋፖር ኩባንያዎችና  ሌሎች በኢትዮጵያ ከተሰማሩ የቢዝነስ ሀላፊዎች ጋርም ተወያይተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን  አጠናቀው በ20ኛው አለም አቀፍ አማካሪ ኮሚቴ ስብሰበ   ለመሳተፍ ትናንት ወደ ደቡብ አፍሪካ  ማምራታቸውን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

ምንጭ፣ ስትሬት ታይም