በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተውን ድርቅ እና ረሀብ ለመከላከል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲደግፍ ኢጋድ ጠየቀ

መጋቢት 10፣ 2009

የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በምስራቅ አፍሪካ በተለያዩ ሃገራት በተከሰቱ የድርቅ እና የፖለቲካ ችግሮች ምክንያት የተፈጠረውን አስከፊ ረሀብ ለመከላከል የቀጠናው ሃገራት እያደረጉ ያለውን ጥረት የአለምአቀፉ ማህበረሰብ እንዲደግፍ ጥሪ አቀረበ፡፡

ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀረበው በአፍሪካ ህብረት ባካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡

ምክር ቤቱ በድርቅ ለተጐዱ እና ረሀብ ውስጥ ላሉ 2ዐ ሚሊየን የሚደርሱ የቀጠናው ህዝቦች እየቀረበ ያለው ድጋፍ እና ሰብዓዊ እርዳታ በቂ አለመሆን እንዳሳሰበው ገልጿል፡፡

የደቡብ ሱዳንን ጉዳይ በጥልቀት ያየው ምክር ቤቱ የአገሪቱ ተቀናቃኞች እ.አ.አ ነሐሴ 2ዐ15 ላይ የተፈራረሙትን የሰላም ስምምነት አለመተግበራቸው አሳሳቢ መሆኑን ገልጾ የቀጠናው ሰላም አስከባሪ ሃይል ወደሃገሪቱ መግባት አስፈላጊ መሆኑን አስምሮበታል፡፡

የሀገሪቱ የሽግግር መንግስት ብሔራዊ አንድነትም ለሃይሉ በፍጥነት ወደሃገሪቷ መግባት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ጥሪ አቅርቧል፡፡

በቅርቡ በሶማሊያ የተካሄደውን ሰላማዊ ምርጫ ያደነቀው ምክር ቤቱ መስመር እየያዘ ያለው የሃገሪቱ ሁኔታ እክል እንዳይገጥመው ለአሚሶም የሚደረገው ድጋፍ በምንም መልኩ መቀዛቀዝ እንደሌለበት አጽንኦት ሰጥቶ ተወያይቷል፡፡

በዘላቂነትም የሃገሪቱን ወታደራዊ ሃይል ግንባታ መደገፍ እና እንዲጐለብት ማድረግ ሃገሪቷን እና ቀጠናውን ከፀጥታ ችግር ያላቅቃል ሲል ገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በተመራው የምክክር መድረክ ላይ ከሁሉም የቀጠናው ሃገራት የተውጣጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም ተወካዮቻቸው ተሳትፈዋል፡፡

በሰለሞን ዳኜ