የኢትዮጵያ እና የጂቡቲ ግንኙነት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡- ጠ/ሚ/ር ኃይለማሪያም

መጋቢት 8፡2009

የኢትዮጵያ እና የጂቡቲ ሁለንተናዊ ግንኙነት በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውህደት በመፍጠር ረገድ በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ትናንት አዲስ አበባ ከገቡት የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌህ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

የሁለቱ አገራት ህዝቦች የጋራ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ አኗኗርና ማህበራዊ እሴቶች አሏቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም በሀገራቱ መካከል በምሳሌነት የሚጠቀስ ግንኙነት መመስረት እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል።

አገራቱ የሁለትዮሽ ንግድ ትብብር፣ ወንጀለኞችን አሳልፎ መስጠትና በወንጀል ጉዳዮች ላይ ህጋዊ ድጋፍ የመለዋወጥ፣ በፍትህ ጉዳዮችና የህግ ስልጠና ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ የመግባቢያ ስምምነቶች ተፈራርመዋል።

ሀገራቱ የመሰረቱትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ እና የደህንነት ጉዳዮች ላይ እንዲያሰፉትም ነው የጠየቁት።

በመንገድ፣ በባቡር፣ በውሃ፣ በሀይል፣ በቴሌኮምና በወደብ ግንባታ መስኮች እያደረጉት የሚገኙትን ትብብርም ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል። 

ፕሬዚዳንት ጌሌህ በበኩላቸው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሳደግ የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት አድንቀዋል።

ሁለቱ አገራት በደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ከቀጠናው አገራት ጋር በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከልና ለተዛማች ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ የኢጋድ አባል አገራት በተቀናጀ ሁኔታ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አለማየሁ ታደለ