የስጋና ወተት የወጪ ንግድ መዳረሻዎችን ለማስፋት እየተሰራ ነው

መጋቢት 2፣2009

ከስጋና ወተት የሚጠበቀውን ገቢ ለማሳደግ የገበያ መዳረሻዎችን ሊያሰፋ መሆኑን የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ ይህን ያለው በትናንትናው ዕለት የስድስት ወር የወጪ ንግድ የዕቅድ አፈጻጸሙን ባቀረበበት ወቅት ነው።

ዋነኛ የገበያ መዳረሻ የሆኑት በመካከለኛው ምስራቅ ዱባይ እና ሳዑዲዓረቢያ ናቸው።

በመሆኑም የገበያ ውስንነት መኖሩና ከዘርፉ የሚጠበቀው ገቢ በተገቢው መንገድ እየተገኘ አለመሆኑ ተገልጿል።

ለዚህም አማራጭ የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት መታቀዱን የኢንስቲትዩቱ የኢንቨስትመንትና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ከሊፍ ሁሴን ገልጸዋል።

የውጭ ገበያ መዳረሻዎች ውስን ሊሆኑ የቻለው የአገሪቱ የእንስሳት ጤና አጠባበቅ ዝቅተኛ በመሆኑና ለስጋ የሚሆኑ እንስሳት በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው ነው ብለዋል።

ስለሆነም በቀጣይ ዓመት ከእንስሳትና አሳ ኃብት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የአገሪቱን የእንስሳት ጤና በማሳደግ በዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊ እንስሳትን በማርባት ስጋን በስፋት ወደሚጠቀሙ የእስያ አገራት በተለይም ወደ ቻይና ገበያ ለመግባት መታቀዱን ነው የገለጹት።

ኢንስቲትዩቱ በግማሽ ዓመቱ ከስጋና ወተት የወጪ ንግድ 79 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዶ 48 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት፤ የዕቅዱን 68 በመቶ ማግኘት ችሏል።

አቶ ከሊፍ እንዳሉት በታቀደው መሰረት ማሳካት ያልተቻለው  ቄራዎች በግብአት እጥረት ምክንያት በአቅማቸው ማምረት አለመቻላቸው፣ የዓለም ገበያ የሚፈልገው የስጋ እንስሳት አለመኖርና ዓለም አቀፍ የገበያ መዳረሻዎች ውስን መሆናቸው ነው።

አገሪቱ በእንስሳት ኃብቷ ከአፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ብትይዝም የእንስሳት ጤና አጠባበቅና የመኖ አቅርቦት ችግሮች በመኖሩ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ገቢ ማግኘት አልቻለችም።

ስለሆነም ለስጋ የሚሆኑ እንስሳትን ለማርባት አስፈላጊውን በማሟላት ዓለም አቀፍ የስጋ ገበያን ሰብሮ በመግባት ከዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ለማግኘት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለገቢ ማነስ ዋነኛው ምክንያት የእንስሳት ጤና አጠባበቅ ችግር በመሆኑ ይህን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የሚገልጹት ደግሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መብረህቱ መለስ ናቸው።

ዶክተር መብራህቱ እንዳሉት ለስጋ የሚሆኑ እንስሳትን የሚያቀርቡ ማህበራትን በስልጠና አቅማቸውን የመገንባት ስራ እየተሰራ ነው።

ምንጭ፡- ኢዜአ