ዓለም ትልቅ ሰብዓዊ ቀውስ ተደቅኖባታል፡- ተመድ

መጋቢት 2፣ 2009

ዓለም ትልቅ ሰብዓዊ ቀውስ እንደተደቀነባት ተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ፡፡

የሰዎችን ህይወት ለመታደግም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፉን እንዲያጠናክር ድርጅቱ ጠይቋል፡፡

በተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ዋና ጸሃፊ ስቴፈን ኦብሪየን እንዳሉት በየመን፣ ሶማሊያ ደቡብ ሱዳንና ናይጄሪያ የሚገኙ 20 ሚሊዮን ሰዎች ረሃብና ድርቅ ተደቅኖባቸዋል፡፡

እንደኦብሪየን ገለጻ ከሆነ ይህን ችግር ለመቅረፍ 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር እስከ መጪው ሰኔ ድረስ ያስፈልጋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከተመሰረተ ወዲህ ቀዳሚ የሆነ ሰብዓዊ  ችግር መከሰቱን ለድርጅቱ አስታውቀዋል፡፡

በአራት ሀገራት የሚገኙ 20 ሚሊዮን ሰዎች በረሃብና ረሃቡ በሚያስከትለው በሽታ ምክንያት ሊሞቱ ይችላሉ ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡

በተከሰተው ችግርም ህጻናት ትምህርት ከማቋረጣቸውም በላይ ሰዎች ቀዬአቸውን እየለቀቁ በመሰደዳቸው አካባቢያቸው ወደ አለመረጋጋት ገብቷል ብለዋል፡፡

ተመድ እስካሁን ከለጋሽ አገራትና ተቋማት 90 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ማግኘቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡