የምስራቅ አፍሪካ ህገ ወጥ ስደትን ለመግታት የቀጠናው አገራት ተቀናጅተው እንዲሰሩ ተጠየቀ

መጋቢት 01 ፣ 2009

በምስራቅ አፍሪካ የሚስተዋለውን ህገ ወጥ ስደትን ለመግታት የቀጠናው አባል አገራት በጋራ ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ተጠየቀ፡፡

በአፍሪካ ቀንድ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት የተዘጋጀና በምስራቅ አፍሪካ የኢጋድ አባል ሃገራት ላይ ባለው ህገ ወጥ ስደት መንስኤና መፍትሄ ላይ ያተኮረ ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሊ ኢሣ አብዲ በምስራቅ አፍሪካ ከምጣኔ ሃብትና ግጭት ጋር ተያይዞ በርካታ ሰዎች ለስደት ይዳረጋሉ፤ እናም ለጋራ መፍትሄ የቀጠናው አባል ሃገራት በፖሊሲዎቻቸው ህገ ወጥ ስደትን መከላከል በሚቻልበት መንገድ በትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

ህገ-ወጥ ስደትን ለመግታት እየተሰሩ ካሉ ስራዎች በተጐዳኝ ህጋዊ የጉዞ አሰራሮችን ማጠናከር፣ ለስደኞች ሰብአዊ መብት መከበር መስራት እና በአካባቢው አገራት መካከል የጋራ ትብብር ይጠይቃል ያሉት ደግሞ የአለምአቀፉ የስደተኞች ተቋም  አይ ኦ ኤም /IOM/ ተወካይ አቶ አሮን ተክለዝጊ ናቸው፡፡

በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በማህበራዊ ጉዳዮች የስደተኞች ጉዳይ አማካሪ ፒተር ሙዱንጊው በበኩላቸው ህብረቱ እንደአህጉር ህገ ወጥ ስደትን ለማስቀረት የሚያስችሉ አጀንዳዎች መቅረፁንና ይህም በቀጣይ የህብረቱ መሪዎች ጉባኤ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር ፤ አማኑኤል ገ/መድህን