ኢትዮጵያ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን የጋራ ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል:-መንግስት

የካቲት 10፣2009

ኢትዮጵያ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተመራጭ እንድትሆን የህዝብና የመንግስት የጋራ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ገለፀ፡፡

ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሚወጡት መረጃዎችን ጠቅሶ ጽሕፈት ቤቱ በሣምንታዊ መግለጫው እንደጠቆመው በተያዘው የበጀት አመት ስድስት ወራት ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የተመዘገበው ካፒታል መጠን 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡

ይህ አፈፃፀም በ2ዐዐ8 በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት እና በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ከተመዘገበው አማካይ አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር በ35 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

እንደ ጽህፈት ቤቱ መግለጫ በአገሪቱ ከዘመናዊ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት ጋር በተያያዘ ባለፉት ስድስት ወራት ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓና ከእስያ አገራት ግዙፍና ታዋቂ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ገብተዋል፡፡

ለአብነትም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ ሶስት የቻይና፣ ሁለት የህንድና የሌሎች አገራት ኩባንያዎች በሃዋሣ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገብተዋል፡፡

አገሪቱ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የእስያ ግዙፍና ታዋቂ ኩባንያዎችን ቀልብ ለመሳብ የቻለችው በአስተማማኝ ሰላሟና መረጋጋቷ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት የተሻለ ተመራጭ ሆና በመገኘትዋ ነው ብሏል መግለጫው፡፡

ይህም ህዝብና መንግስት ለአመታት ባደረጉት የልፋት ውጤት የተገኘ እንደሆነ ነው ያስቀመጠው፡፡

በተያዘው የተሃድሶ እንቅስቃሴም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለዘለቄታው በመፍታት የኢንዱስትሪ ልማታችን ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር ለሆኑት የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች የተሻለ የኢንቨስትመንት አማራጭ መሆናችንን እንቀጥላለን ብሏል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ለኢቢሲ በላከው ሳምንታዊ መግለጫው፡፡