የወጣቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

የካቲት 10፣2009

ወጣቶችን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በዘላቂነት ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡

የክልሎችና የከተማ አስተዳድሮች የወጣቶች ፈንድ አጠቃቀም መመሪያና አሠራር ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት በአዳማ ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ የወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎች የመንፈቅ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ገምግሞ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ተቀምጧል።

ሚኒስቴሩ በግምገማው በከተሞቹና በክልሎች እየተከናወኑ የሚገኙ መልካም ጅምሮች እንዲጠናከሩና ክፍተቶች እንዲታረሙ አስገንዝቧል።

የወጣቶችና ስፖርት ሚንስትር ርስቱ ይርዳው ስራ አጥ ወጣቶችን በመለየትና በማደራጀት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሙያ ምሩቃንና ከዛ በታች የትምህርት ዝግጅት ላላቸው ስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ  የተደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ወጣት ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ወጣቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ የተሰራው ስራ አመርቂ አለመሆኑን ጠቅሰው ትኩረት ሰጥቶ መስራት ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።

ሚንስትሩ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፖርኮች ወጣቶች ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ማመቻቸት ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል።

ከስራ ዕድል ፈጠራ ባሻገርም የስፖርት ማዘውተሪያና የወጣት ማዕከላትን የማስፋፋቱ ተግባር ሊጠናከር እንደሚገባም አውስተዋል።

ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን አስመልክቶ በተለይም ክልሎች ለወጣቶቻቸው ስልጠና በመስጠት ግንዛቤ ለማስጨበጥ አበክረው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አክለዋል።

ሚኒስቴሩ "ሰፊ ተሳትፎና ቀጣይ እንቅስቃሴ ለንቁ ትውልድ" በሚል መሪ ሃሳብ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎችና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር አዳማ ላይ ለአራት ቀናት ሲያካሂድ የቆየው ምክክር መጠናቀቁን ኢዜአ ዘግቧል።