ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካን ትብብር ለማጠናከር ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች መሆኗን ገለጸች

የካቲት 10፣2009

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትብብር ለማጠናከር  ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች መሆኗን የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በተቋሙ የለውጥና የጥልቅ ተሀድሶ እንቅስቃሴ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሚኒስቴሩ  በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትብብሮች እንዲጠናከሩ እየሰራ ነው ብለዋል።

በሶማሊያ የተሳካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መከናወኑ የደቡብ ሱዳን ፖለቲካዊ ቀውስ ለማሻሻል የሚደረጉ ጥረቶች መቀጠላቸው በፖለቲካ የሚጠቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሚንስትሩ  ከኬንያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን እና ኡጋንዳ ጋር ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመገንባት ላይ መሆኑን ገልጸው  በዚህም ኢትዮጵያ  ለቀጣናው ብልጽግና የበኩሏን እያበረከተች ነው ብለዋል።

ዶክተር ወርቅነህ ከአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን በተደረገው የኢትዮጵያና የግብጽ የመሪዎች ውይይት የአባይ ውሀ አጠቃቀም ጉዳይ ላይ ምክክር በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱንም አስታውሰዋል።

ገበየሁ የአባይ ውሃ የተፋሰሱ ሀገራት የትብብር ማእከል እንዲሆን የሚደረገው ጥረት መጠናከሩንም ሚንስትሩ ገልፀዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና በአውሮፓውያኑ አዲሱ አመት ስራ የጀመረችው ኢትዮጵያ በሁለት አመታት ቆይታዋ የአፍሪካን ሰላምና ብልጽግና ላይ አተኩራ እንደምትሰራም ሚንስትሩ አስታውቀዋል።

ሪፖርተር:-ፍትህአወቅ የወንድወሰን