በኢትዮጵያ ዙሪያ በርካታ ጥናታዊ ፅሁፎችን ያበረከቱት ፕሮፌሴር ሪቻርደ ፓንክረስት ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

የካቲት 9፣2009

በኢትዮጵያ ዙሪያ በርካታ ጥናታዊ ፅሁፎችን ካበረከቱት ተመሪማሪዎችና የታሪክ ፀሀፍት መካከል ታዋቂ የሆኑት ፕሮፌሴር ሪቻርደ ፓንክረስት ከዚህ አለም በሞት ተለዩ፡፡

ኢትዮጵያ የጣልያንን ወረራ በመመከት ላይ ሳለች ለሃገሪቱ ደጋፊ የነበሩት የሲልቪያ ፓንክረስት ልጅ የሆኑት የታሪክ ተመራማሪ ሪቻርድ ፓንክረስት ወደ ኢትዮጵያ ከመጡበት ከ1956 ጀምሮ ህይወታቸውን ለኢትዮጵያ ታሪክ ለመዘከር የሰጡ ናቸው፡፡

ከ2ዐ በላይ መፅሀፎችን የፃፉና በኢትዮጵያ ታሪክ ባህል እና ምጣኔ ሃብት ዙሪያ የቀረቡ በርካታ ፅሁፎችን ያዘጋጁ ናቸው፡፡ እኝህ ምሁር የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም መስራች ዳይሬክተር እና ከኢትዮጵያ ወዳጆች መካከልም በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሣሉ፡፡

የአክሱም ሀውልትን ለማስመለስ በተደረገው ጥረት ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ሲሆን ለዚሁ አስተዋጽኦቸው ከኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ሽልማት ተበርክቷላቸዋል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የደረጉት አስተዋጽኦ ከእንግሊዝ መንግስትም እንዲሁ ሽልማት አግኝተዋል፡፡

የኢፌድሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር በዶክተር ፓንክረስት ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልፀዋል፡፡

የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም ሰኞ በ9፡ዐዐ ሰአት በቅዳስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስትያን በታላቅ ስነ ስርዓት እንደሚፈፀም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የላከው መረጃ ያመለክታል፡፡