የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ አዋጆችን ፣ተጨማሪ በጀትና ሹመት በማጽደቅ ተጠናቀቀ

 የካቲት 9 ፣2009

 የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ሶስት አዋጆችን፣ ተጨማሪ በጀትና ሹመት በማጽደቅ ተጠናቀቀ፡፡

ጉባኤው ዛሬ ያጸደቃቸው አዋጆች የታክስ አስተዳደር፣ የከተሞች አስተዳደርና የገቢ ግብርን የተመለከቱ ናቸው፡፡

የክልሉ ታክስ አስተዳደር ስርዓት ራሱን ችሎ የበለጠ ቀልጣፋና  ውጤታማ እንዲሆን  የታክስ አስተዳደር አዋጁ መውጣቱ ተገልጿል፡፡

አዋጁ በታክስ ህጎች አተረጓጎም ረገድ በታክስ አስተዳደሩ ውስጥ በሚፈጠር ልዩነት ምክንያት ታክስ ከፋዩ ሲያጋጥመው የነበረውን እንግልት በማስቀረት ወጥነት ያለው  እንዲሆን ያስችላል፡፡ 

የከተሞች አስተዳደር አዋጅ ደግሞ በክልሉ  መልካም አስተዳደርን ለማስፈንና ሁሉን አቀፍ ልማት በማረጋገጥ ከተሞች የምርት የአገልግሎትና የገበያ ማዕከላት ሆነው የክልሉን ኢንዱስትሪ ልማት ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያስችል ተመልክቷል፡፡

እንዲሁም የገቢ ግብር አዋጅ የግብር አከፋፈል ስርዓቱ ፍትሀዊነት ያለው እንዲሆንና ግብር የማይከፈልባቸውን ገቢዎች በግብር መረብ ውስጥ ለማስገባት እንደሚያስችል በጸደቀው አዋጅ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡

የክልሉ ኢኮኖሚ ዕድገት ከደረሰበት ደረጃ ጋር የተጣጣመና ኢኮኖሚውን የሚያግዝ ዘመናዊና ቀልጣፋ የግብር ስርዓት ለመዘርጋት በማስፈለጉ አዋጁ መውጣቱ ተጠቁሟል፡፡

የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር የስራ ቆይታቸው በማብቃቱና የስራ መልቀቂያ በማስገባታቸው በቦታቸው አቶ ተስፋዬ ታፈሰን ዋና ኦዲተር በማድረግ ምክር ቤቱ ሾሟል፡፡

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የቦርድ አባል በነበሩት ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን ምትክ አቶ ሰለሞን ኃይሉ እንዲተኩም ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡

የሀድያ ብሔረሰብን ወክለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካይ እንዲሆኑ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤልን ምክር ቤቱ ወክሏል፡፡

ምክር ቤቱ የተሰጣቸውን የዳኝነት ስልጣን ለግል ጥቅም በማዋል በስነ ምግባር ጉድለት ምክንያት 18 ዳኞችን እንዲነሱ ሲያደርግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ለከፍተኛ ፍርድ ቤትና ለወረዳ ፍርድ ቤቶች የ116 ዳኞችን ሹመት አጽድቋል፡፡  

በተጨማሪም ለመምህራን የደሞዘ ጭማሪ በክልል ማዕከል ለሚገኙ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ፣ለተለያዩ ኮሌጆችና ሌሎችን ተግባራት የሚውል ከአንድ ቢሊዮን 682 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት በማጽደቅ ጉባኤው መጠናቀቁን  ኢዜአ  ዘግቧል፡፡