የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በሀላባ ልዩ ወረዳ የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ከንባታ ጠንባሮ ዞን ገብቷል

የካቲት 09፣ 2009

የታላቁ ህዳሴ ግድብ  ዋንጫ በሀላባ ልዩ ወረዳ የነበረውን  ቆይታ አጠናቆ ቀጣዩ መዳረሻውን ከንባታ ጠንባሮ ዞን  ለማድረግ ዳምቦያ ወረዳ ገብቷል፡፡

የዞኑ ነዋሪዎች ለዋንጫው ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል፡፡ዋንጫው  ወደ ዞናቸው በመምጣቱ ደስተኛ መሆናቸውንና  ድጋፋቸውን አጠናክረው  እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡

በዋንጫው አቀባበል ስነ  ስርዓት  ላይ የተገኑኙት  የደቡብ ክልል  ምክትል  ርዕሰ  መስተዳድር  አቶ  መለሰ  አለሙ  የህዳሴው ግድብ  ዋንጫ የኢትዮጵያ  ህዝቦች ድህነትን   በአንድነት ለማሸነፍ  የሚያደርጉትን  ጥረት   የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የዞኑ ህዝብ  ቀደም ሲል  ለግድቡ ግንባታ  ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋና ያቀረቡት  ምክትል ርዕሰ   መስተዳድሩ፣ በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

በከንባታ ጠንባሮ ዞን ለግድቡ ግንባታ እስከ አሁን  30 ሚሊዮን ብር  ተሰብስቧል፡፡ዋንጫው ከወረዳ ወረዳ  እየተዘዋወረ በሚያደርገው የ18 ቀናት  ቆይታው ደግሞ ተጨማሪ 40 ሚሊዮን ብር  ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የደቡብ  ሬድዮና ቴሌቪዥን ለኢቢሲ በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡