በድርቅ የተጐዱ አርብቶ አደሮች መንግስት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ

የካቲት 8፣2009

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በድርቅ የተጐዱ አርብቶ አደሮች መንግስት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ፡፡

ፕሬዝዳንቱ በክልሉ በፋፈን ዞን ጉብኝት አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በፋፈን ዞን የቀብሪ ከሀ ቀበሌ በክልሉ በድርቅ ከተጎዱ አከባቢዎች አንዷ ናት።

የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ  በቀበሌዋ ተገኝተው ተጎጂዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ተመልክተዋል።

ከፕሬዝዳንቱ ጋር የተወያዩት የአከባቢው ማሕበረሰብ ተወካዮች አከባቢው በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቃ መሆኑን ገልጸው በመንግስት እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ የችግሩን አስከፊነት እንደቀነሰው ተናግረዋል።

አሁን ላይ ሁኔታዎች እየተባባሱ በመምጣታቸው የመንግስት ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ  የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልን ጨምሮ ሌሎች የአርብቶ አደር አከባቢዎችም ድርቅን በዘላቂነት መቋቋም እንዲችሉ አካባቢያቸውን በማልማት እንዲሳተፉ አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት የድርቁ ሁኔታ አለም አቀፍ ገጽታ የተላበሰ በመሆኑ  የተረጂዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ  ይህም ከአለም አቀፍ አጋሮች የሚጠበቀውን ድጋፍ ውሱን እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ድርቁ በሰው ህይወትም ሆነ በእንሳሳት ላይ የሚያደርሰውን የከፋ ጉዳት ለመከላከል በመንግስት በኩል የሚደረገውን ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ሪፖርተር:-ደረጀ ጥላሁን (ከጅግጂጋ)