የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ በአለም አደባባይ ደምቃ እንድትታይ ያደረገ መሆኑ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ

የካቲት 8፣2009

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ባህል እና እሴቷን ጠብቃ በአለም አደባባይ ደምቃ እንድትታይ ያደረገ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዶክተር ሂሩት ወልደ ማርያም ገለጹ፡፡

121ኛው የዓድዋ የድል ቀንን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ለማክበር ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው፡፡

የዘንድሮው 121ኛው የአድዋ ድል በዓል የአድዋ ድል ብዝሀነትን ላከበረችው ኢትዮጵያ ድህነትን ለማሸነፍ የሚያስችል ህያው አብነት ነው በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የባህልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶተር ሂሩት ወልደ ማርያም ተናግረዋል፡፡

ሚንስትሯ የአድዋ ድል በዓል የአይቻልም መንፈስን የሰበረና ኢትዮጵያ ባህልና እሴቷን ጠብቃ እንድትኖር ያደረጋት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የአድዋ ድል በዓልን ከመዘከር ባለፈ የቱሪስት መስህብ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ህዝቦችን ባርነት ከፈጣሪ የተቸራቸው መሪር ዕድላቸው አድርገው ይቆጥሩ በነበረበት ዘመን ኢትዮጵያን ለመውረር የመጣው የጣሊያን ወረሪ ሀይል ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ዓድዋ ላይ ድልን በመቀናጀት ወደ መጣበት መልሰውታል። የድል ቀኑም በየዓመቱ የካቲት 23 ይከበራል፡፡

የዘንድሮ 121ኛው የዓድዋ የድል ቀንም የፊታችን የካቲት 23/2009 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ ተከብሮ ይውላል፡፡

ሪፖርትር፡-ሰለሞን ፀጋዬ