የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሣኝ መሆኑ ተገለፀ

ጥር 04፣ 2009

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአገሪቱ ጠረፍ አካባቢ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል በሚደረገው ትግል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሣኝ መሆኑን ገለፀ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በጅቡቲ ጠረፍ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የስራ እንቅስቃሴም ጎብኝቷል፡፡

በመስክ ምልከታውም በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የሚሰሩ ሰራተኞች ሙቀትን ጨምሮ ሌሎች ችግሮችን ተቋቁመው በ3 ፈረቃ 24 ሰአት በቁርጠኝነት መስራታቸውን ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ አንስቷል፡፡

ይሁን እንጂ ሰራተኞቹ ለፍተሻ የሚጠቀሙበት መሣሪያ በጨረር የሚሰራ በመሆኑ የሰራተኞቹን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ የጨረር መከላከያ አልባሣት ሊሟላላቸው እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው ጠቁሟል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መሪ አቶ አባቡ ብርሌ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የስራ አፈፃፀም መሻሻል ቢያሣይም የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ግን የኮንትሮባንድ መነሻ ከሆኑ አገራት ጋር በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ባለፉት ስድስት ወራት በፍተሻ ከተያዙ ንብረቶች ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ማግኘት ችሏል፡፡

በኮንትሮባንድ ከተያዙ እቃዎች መካከል ደግሞ አልባሣት፣ የምግብና የንፅህና መጠበቂያ እና ሌሎች ቁሳቁሶች እንዳሉ ተገልጿል፡፡ ዘገባው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ነው፡፡