ድርቅን ለዘለቄታው በራስ አቅም ለመቋቋም ርብርብ እንደሚያስፈልግ መንግስት አስታወቀ

ጥር 03፣ 2009

ድርቅን ለዘለቄታው በራስ አቅም ለመቋቋም ርብርብ እንደሚያስፈልግ መንግስት አስታወቀ።

የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለኢቢሲ የላከው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ ድርቅን ለዘለቄታው በራሣችን አቅም ለመቋቋም እንረባረብ ይላል፡፡

ባለፈው አመት በሃገር ደረጃ ከባድ ድርቅ አጋጥሞ እንደነበር ያስታወሰው መግለጫው፣ የኢፌዴሪ መንግስት ችግሩን በራስ አቅም ለመፍታት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በተደረገ ርብርብ ሰብአዊ ቀውስ ሳይደርስ ችግሩን መቋቋም ተችሏል ብሏል፡፡

ዘንድሮም በአንዳንድ የሃገሪቱ ቆላማ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ድርቅ ማጋጠሙን ያተተው መግለጫው፣ የገጠመውን ችግር ለመቋቋም የፌዴራል እና የክልል መንግስታት ብሎም ህዝቡ የጋራ ርብርብ እያደረጉ እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

በዚህም ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች እየቀረቡ ሲሆን በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች የሚኖሩ የአርብቶ አደር ልጆችም ከቀያቸው ሳይርቁ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ እየተደረገ ነው ብሏል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በመግለጫው፡፡

ድርቅን ለመቋቋም የሚያስችል የተፋሰስ ልማት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን በመግለፅ መንግስት የተከሰተውን ድርቅ በጊዜያዊነት ለመፍታት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል ያለው መግለጫው ህዝቡ ድርቁን በዘላቂነት ለመቋቋም እያደረገ ያለውን የነቃ ተሣትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡