ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ተወዳዳሪ እንድትሆን የህብረት ስራ ማህበራት ሚና እንዲጎለብት ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ አሳሰቡ

የካቲት 01 ፣2009

ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ የምትሳተፍባቸው ምርቶች በጥራታቸው የተሻሉና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል የህብረት ስራ ማህበራት በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ፡፡

አራተኛው አገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚዬም "የህብረት ሥራ ማህበራት ግብይት ለዘላቂ ልማታችን ስኬት" በሚል መሪ ቃል በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ተከፍቷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኤግዚቢሽኑን ሲከፍቱ እንዳሉት መንግስት ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ለቀረጻቸው ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተግባራዊነትና ለተመዘገበው ፈጣን ዕድገት ስኬት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሚና የጎላ ነው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲኖርና ተወዳዳሪ የወጪ ንግድ ለመገንባት ማህበራቱ ለጥራት ትኩረት ሰጥተው መሳተፍ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

መክፈቻው ላይ ሞዴል ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተሞክሮና ስኬቶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል።

አራተኛው የህብረት ሥራ ማኅበራት ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚዬም ከየካቲት 1 እስከ የካቲት 8 ቀን 2009 ዓም በኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል።

 ሪፖረተር ፥ ተስፋዬ ለሜሳ