የቀድሞው የሶማሊያ ጠ/ሚ ሙሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ቀጣዩ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

የካቲት 01 ፣2009

የቀድሞው የሶማሊያ ጠቅላይ ሚንስትር ሙሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ  ቀጣዩ  የአገሪቱ  ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ።

ቀጣዩን የሶማሊያ ፕሬዝዳንት የመምረጥ መብት ያላቸው የአገሪቱ  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥበቃው  በተጠናከረበት ሞቃድሾ አየር ማረፊያ ተገኝተው  ድምፃቸውን ሲሰጡ ውለዋል።

ዛሬ በተካሄደው  ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ 20 ዕጩዎች ቀርበው የቀጣይ ሶማሊያ ፕሬዝዳንት ለመሆን ወደ  ሁለተኛው ዙር የማጣሪያ ምርጫ አልፈው የነበሩት በስልጣን ላይ ያሉት ሀሰን ሼህማህሙድ 88፣ሙሐመድ አብዱላሂ  ፋርማጆ  72፣ ሼሪፍ ሼህ አህመድ  49 እና ኦማር አብዱራሽድ 39 የሶማሊያ የህዝብ እንደራሴዎችን ድምፅ በማግኘት ነው።

ይሁን እንጂ በሁለተኛው ዙር በተካሄደ   የማጣሪያ  ምርጫ ከአራቱ   እጩዎች ሶማሊያን በጠቅላይ ሚንስትርነት ሲመሩ  የነበሩት ሙሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ማሸነፋቸው ተመልክቷል።

ቢቢሲ ከቦታው እንደዘገበው ተጠብቀው የነበሩት በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼህ ማህሙድ ለሶስተኛ ዙር ምርጫ  ሳይካሄድ በውጤቱ መስማማታቸውን ገልፀዋል።

ሶማሊያዊያን  ምርጫው በሰላም በመጠናቀቁ ደስታቸውን ገለፀዋል። ደስታቸውንም በአደባባይ በመግለፅ ላይ ናቸው ተብሏል።

ከምርጫው በፊት ራሳቸውን ያገለሉት ብቸኛዋ ሴት ፕሬዝዳንታዊ እጩ የቀድሞው የሶማሊያ ጠቅላይ ሚንስትር ሙሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ  ቀጣዩ  የአገሪቱ  ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው ለመፈራረስ ድናለች ብለዋል።

የምርጫውን መካሄድ ተከትሎ በዋና ከተማዋ ምንም አይነት  የየብስም ሆነ  የአየር ትራፊክ እንቅስቃሴ  እንዳይኖር እገዳ ተጥሏል፤ትምህርት ቤቶችም ተዘግተው ነውየዋሉት።ይህም ምርጫውን ሊያሰናክል የሚችል  የሽብር ጥቃት እንዳይከሰት ለማድረግ መሆኑን ቢቢሲ ከስፍራው ዘግቧል።

ምርጫው በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ  የኖረችውን  ሶማሊያ ጠንካራ  ማዕከላዊ  መንግስት እንዲኖራት የሚያደርግ ነው በሚል  ተስፋ  ተጥሎበታል።