አዲሱ የኤርታሌ እሳተ ጎመራ አስፈላጊው የአካባቢ ጥበቃ እንደሚደረግለት የአፋር ክልል አስታወቀ

የካቲት 01 ፣2009

በቅርቡ  የተከሰተው አዲሱ የኤርታሌ እሳተ ጎመራ አስፈላጊው የአካባቢ ጥበቃ እንደሚደረግለት የአፋር ክልላዊ  መንግስት አስታወቀ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሐጂ ስዩም አወል እንደተናገሩት ከነባሩ ኤርታሌ በተጨማሪ አዲስ የተፈጠረው እሳተ ገሞራ የአካባቢ ጥበቃ በማድረግ የቱሪስት መስህብነቱን ለማሳደግ ይሰራል ብለዋል።

በደቡብ ምስራቅ ኤርታሌ ተከስቶ የነበረው ይኸው እሳተ ገሞራ የከፋ ጉዳት እንደማያስከተልም በአዲስአበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ-ምድር ትምህርት ቤት የስትራክቸራል ጂኦሎጂ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ኪዳኔ ገልፀዋል።

በአርታሌ ዙሪያ ተከስቶ የነበረው እሳተ-ገሞራ አነስተኛ በመሆኑ ወደፊት ጉዳት አያስከትልም ብለዋል።

በእሳተ ገሞራ ሂደት የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የመሬት መዛነፍና መስመር የሚሰሩ የመሬት ቅርጾች የመፈጠር ምልክቶች እንደሚታዩ የገለጹት ፕሮፌሰሩ፣ ይህም የአፍሪካና የዓረቢያ ልሳነ ምድር የመነጣጠል ውጤት ነው ብለዋል።

በኤርታሌ  ጉብኝት ላይ የነበሩ ጎብኝዎች  በበኩላቸው ኤርታሌን በምሽት በመጎብኘታቸው ፍፁም ደስታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። በመስህብነቱም ቀልባቸውን እንደሳበው ገልፀዋል። 

ሪፖረተር ፥ አባዲ ወናይ