የወጪ ንግድ ማነቆዎችን ለመፍታት ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

የካቲት 01፣2009

በወጪ ንግድ ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ሁሉም አካላት የድርሻቸውን ተግባር በአፋጣኝ እንዲያከናውኑ ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡

ብሔራዊ የኤክስፖርት አስተባባሪ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ባካሄደው ቀጣይ ስብሰባ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ በሥጋ እና በቁም እንስሳት ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰብሳቢነት የጋራ ውይይት አካሂዷል፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በሀገሪቱ መዋቅራዊ ሽግግር እንዲኖር በአብዛኛው ግብርና መሠረት ያደረገውን ኢኮኖሚ ወደ ማምረቻ ዘርፍ ለማሸጋገር ይህን ተከትሎም የማኑፋክቸሪንግ ወጪ ንግድ ከአግሮ ፕሮሰሲግ ጀምሮ ያለውን መጠንና ጥራት ለማሣደግ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ ሥራዎች ሲገመገሙ ኤክስፖርቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሣደጉ ከመሄድ ይልቅ መጠኑ እየቀነሰ በመሄዱ ይህን ጉድለት ለማስተካከል አካሄዱን መቀየር ተገቢ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡

በዚህ መሠረት በኤክስፖርቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ከሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ባለሀብቶች፣ የማህበር አባላት፣ ዘርፉን ከሚመሩ አስፈፃሚ አካላትና የተለያዩ የመንግስት ሃላፊዎች ጋር የጋራ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ወቅት አገሪቱ ካላት እምቅ የእንስሳት ሀብት አንፃር ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳላገኘች ተጠቅሶ ይህን ገጽታ ለመቀየር ውጤታማነትን መሠረት ያደረገ ሥራ መከናወን እንዳለበት ተቀምጧል፡፡

ከዚህ አንፃር የኤክስፖርት ዘርፉን ለማጎልበት እና የሚታዩ ዋና ዋናማነቆዎችን ለመፍታት በመንግስት እና በባለሃብቶች በኩል ምን ምን ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው ሰፊ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ዋና ዋና ማነቆወችን ማለትም የአቅርቦት ችግሮች፣ ከጉምሩክ እና ታክስ ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ ከቁም እንስሳት ጋር ተያይዞ የሚታየውን የኮንትሮባንድ እና ከምርትና ከምርታማነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለማስወገድ የሚሰችሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተሰጥተዋል፡፡

በዚህም መሰረት በኤክስፖርት ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች የቫት ተመላሽ በሰባት ቀናት ውስጥ እንዲከፈላቸው፣ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በCAD / Cash against development / ጥሬ ዕቃ ለማስገባት ሲጠየቅ ያለምንም ገንዘብ ማስያዣ እንዲያስገቡ፣ መንግስት የኮንትሮባንድ ንግድን በአስቸኳይ እንዲገታ እንዲያደርግ እና ከሎጀስቲክስ ጋር የተያያዙ ችግሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ኃላፊነቱን ወስዶ እንዲያስፈፅም፣ በጥሬ ቆዳና ሌጦ የተጣለው ቫትም እንዲነሣ ስምምነት ላይ መደረሱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የላከልን መረጃ ያመለክታል፡፡