የተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራሙ ለእናቶችና ህጻናት ሞት መቀነስ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ተገለጸ

ጥር 10፣2ዐዐ9

በአገሪቷ ስድስት ክልሎች የተተገበረው የተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም ለእናቶችና ህጻናት ሞት መቀነስ ወሳኝ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ።

ይህ የተገለጸው የፕሮጀክቱን መጠናቀቅ አስመልክቶ በተካሄደ አውደ ጥናት ነው።

ፕሮግራሙ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ለስምንት ዓመታት የቆየ ሲሆን 37 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጓል።

በአማራ፣ ደቡብ፣ ትግራይና ኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ 300 ወረዳዎች እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በሶማሌ ክልሎች የተወሰኑ ወረዳዎች ነው የተተገበረው። 

በጤናው ዘርፍ ጥራት ያለው አገልግሎትና እንክብካቤ ማጠናከር፣ የማህበረሰቡን በህክምና ተቋማት የመጠቀም ባህል ማሳደግና የዘርፉን  የሰውና የተቋም አቅም ማጎልበት የፕሮግራሙ ዋነኛ ዓላማዎች ናቸው።

የጤና ጥበቃ ሚንስትር ዴኤታ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ዳንኤል ወልደ ሚካኤል እንደተናገሩት ፕሮግራሙ ለእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ የጎላ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ከአምስት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካይ 16 ሺህ ህጻናትና 178 ሺህ እናቶች ይሞቱ እንደነበርና በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ ወደ 10 ሺህ ዝቅ ማለቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ነፍሰ ጡር እናቶች ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ እንዲወልዱ በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የተሰራው ስራ ውጤታማ እንደሆነም ገልጸዋል። 

ለጤና ባለሙያዎች የተሰጡ ስልጠናና የቴክኒክ ድጋፎች እናቶች በወሊድ ወቅት የሚያጋጥሟቸውን የጤና ችግሮች የመከላከል አቅማቸውን አሳድገውታልም ብለዋል።

በፕሮግራሙ በተሰሩ ስራዎች በገጠሩ የአገሪቷ ክፍል የሚገኘው ህብረተሰብ የህክምና ተቋማትን የመጠቀም ባህል እያደገ መምጣቱንም አክለዋል።

የተቀናጀ የቤተሰብ ልማት ፕሮግራም ኃላፊ ዶክተር መንግስቱ አስናቀ በበኩላቸው ፕሮግራሙ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል።

እናቶች የወሊድ መቆጣጠሪያ እንዲጠቀሙና የቤተሰብ ምጣኔ እንዲያድግ ማድረጉን ጠቅሰው የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ለፕሮግራሙ ስኬት ሚና እንደነበረው መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።