የአለማችን ትልቁ አውሮፕላን ሁለተኛ የበረራ ሙከራው ከሸፈ

ነሐሴ 18፣ 2008

በባሉን ቅርፅ የተሠራው የአለማችን ትልቁ አውሮፕላን በሁለተኛ የበረራ ሙከራ አደጋ ደረሰበት።

25 ሚሊዮን ፓውንድ የፈሰሰበት ይሄው አውሮፕላን በመጀመሪያ በረራው ስኬታማ ሙከራ ካካሄደ በሃላ ነበረ በሁለተኛ የበረራ ሙከራ መሬት ላይ ሊያርፍ ሲል በአብራሪዎቹ  አካባቢ ባለው የአውሮፕላኑ  ክፍል አደጋው የደረሰበት፡፡

በአደጋውም በአውሮፕላኑ ላይ የነበሩ ሁሉም ባለሞያዎች ምንም ችግር ሳይደርስባቸው መትረፋቸው ነው የተነገረው፡፡

ኤርላንደር ተብሎ የተሠየመውና በባሉን ቅርፅ የተሠራው አውሮፕላን 92 ሜትር ርዝመት አለው፡፡  

በመጀመሪያ የበረራ ሙከራው አውሮፕላኑ እንግሊዝ ሃገር ከሚገኘው የካርሊንግተን አውሮፕላን ጣቢያ በመነሳት ለ2ዐ ደቂቃ ያህል በሯል፡፡

በ16ሺ ጫማ ከፍታ በሰአት 9ዐ ማይል መብረር የሚችለው የአለማችን ትልቁ አውሮፕላን ብዙ ጭነት መሸከም የሚችልና ነዳጅ ቆጣቢም ነው ተብሏል፡፡

አውሮፕላኑ ለስለላ ስራ፣ ለኮሚኒኬሽን፣ ለእርዳታ አቅርቦት እንዲሁም መንገደኞችን ለማጓጓዝ እንደሚረዳ ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ለንግድም ሆነ ለወታደራዊ አገልግሎት ተስማሚ ሆኖ እንደተሠራ አውሮፕላኑን ያመረተው የሀይብሪድ ኤይር ቬክል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኤምሲ ግሌርስ ተናግረዋል፡፡

አምራቹ  ኩባንያ አሻሽሉ በማምረት  ከስድስት አመት በኃላ ለገበያ  እንደሚያቀርበው አመልክቷል።

ምንጭ ፥ ቢቢሲ