34 ዓመታት በዘለቀው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ እና ኬንያ ተፎካካሪነት

ነሐሴ 8 ፣2009

ለ10 ቀናት ያህል  በለንደን ሲካሄድ የሰነበተው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአሜሪካ የበላይነት ተቋጭቷል፡፡ ኬንያ ከአፍሪካ ቀዳሚ ስትሆን ከዓለም ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡ ከአፍሪካ እንደ ርዝመት ዝላይና አጭር ርቀት ባሉት ዘርፎች ጭምር በአዲስ መልክ በዘንድሮው ሻምፒዮና ብቅ ያለችው ደቡብ አፍሪካም ከአለም በሶስተኝነት ከአፍሪካ ደግሞ ኬንያን ተከትላ ፣ኢትዮጵያን ደግሞ አስከትላ በሁለተኝነት ጨርሳች፡፡

ኢትዮጵያ በለንደኑ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድሩን ከአፍሪካ ሶስተኛ ከዓለም 7ኛ ሆና ነው የጨረሰችው፡፡

በለንደኑ ሻምፒዮና  አልማዝ አያና እና ሙክታር እንድሪስ ወርቅ አግኝተዋል፡፡ ታምራት ቶላ ፣ አልማዝ አያና እና  ጥሩነሽ ዲባባ ደግሞ የብር ሜዳሊያዎችን አስገኝተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ሻምፒዮናው ያስመዘገበችው ውጤት ካለፉት 9 ሻምፒዮናዎች የሚሻለው ከሁለቱ ብቻ ነው፡፡ ይህም ከበርሊን እና ዴጉ ሻምፒዮና ነው፡፡

የዘንድሮው ውጤት ከቅርቦቹ ከሞስኮው /እ.አ.አ ከ2013ቱ/ እና ከቤጅንግ /የ2015ቱ/ ሻምፒዮናዎች ያነሰ ውጤት ነው፡፡በቤጅንጉ ሻምፒዮና ኬንያ ከአለም ቀዳሚ በመሆን  የዓለም ሻምፒዮን ሆና ማጠናቀቋም ይታወሳል፡፡

በሄልስንኪው ሻምፒዮና /እ.አ.አ 2005/ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው 3 ወርቅ፣ 4 ብር እና 2 ነሐስ በሻምፒዮናው ታሪክ የምንግዜውም ምርጡ ነው፡፡

ይህ ወቅት ጥሩነሽ ዲባባ ድርብ ወርቅ ያገኘችበት፣ የቀነኒሳ በቀለ፣ መሰረት ደፋር እና ስለሽ ስህን  ወርቃማ እግሮች ዓለምን ያስጨበጨቡበት ነው፡፡

ሻምፒዮናው በተደጋጋሚ በጎረቤታሞቹ ኢትዮጵያ እና ኬኒያ መካከል ከባድ ፉክክር የሚያስተናግድ ሆኖ ታይቷል፡፡

ነገር ግን በሻምፒዮናው ታሪክ ኬኒያውያን ፍፁም የበላይነትን አሳይተዋል፡፡ ከ16ቱ ሻምፒዮናዎች ኬኒያውያን በ12ቱ ከኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት አግኝተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከኬኒያ በልጣ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ መገኘት የቻለችው በ4ቱ ሻምፒዮናዎች ብቻ ነው፡፡

በወርቅ ሜዳሊያ ስናነፃፅረው ደግሞ ካለፉት 9 ሻምፒዮናዎች ኬኒያ 37 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማንሳት ስትችል፣ ኢትዮጵያ 22 ወርቅ ነው ማግኘት የቻለችው ፡፡ ይህ ውጤት በኦሎምፒክ ውድድርም የሚቀራረብ ነው፡፡

ኬኒያውያን አዳዲስ የውድድር ዓይነቶችን እና አዳዲስ ሜዳሊያዎችን በየመድረኩ ማግኘት እየቻሉ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለመዱ ርቀቶችን እንኳ ማሸነፍ እየተሳናት ነው፡፡

በመሆኑም በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያ እና ኬንያ ፉክክር በስም ብቻ ከመቅረቱ በፊት  ሊሰራ እንደሚገባ ውጤቶቹ ማሳያ ናቸው፡፡

ልዩነቱ እ.ኤ.አ ከ1983ቱ ከሄልሲንኪው የመጀመሪያው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ ዘንድሮው የለንደኑ መድረክ የዘለቀ ነው፡፡

በከበደ ባልቻ በማራቶን የተገኘው የአንድ ብር ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ  ስም የነበረ ቢሆንም ኬንያ ያኔ ሜዳሊያ ሰንጠረዥ እንኳን መቀላቀል አልቻለችም ነበር፡፡

አሁን ላይ ግን ኬንያ የመወዳሪያ ዘርፏን እያሰፋችና ጥራት ላይ እየሰራች በመምጣቷ ሁሌም ከኢትዮጵያ ፊት የምትቆም አገር ሆናለች፡፡የዘንድሮው የ5 ወርቅ ፣2 ብርና 4 ነሀስ ሜዳሊያ ለዚሁ ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከ16 የአለም ሻምፒዎናዎች በኃላ ሁለት ወርቅን ጨምሮ ያገኘችው 5 ሜዳሊያ በሰንጠረዡ  የኬንያ ተከታይ አድርጓታል፡፡

ዛሬ ላይ ኬንያ የቤጂንጉን ከአለም የአንደኝነት ድሏን መድገም ባትችልም በለንደኑ የአለም የሻምፒዮናው ቁንጮ  አሜሪካን በመከተል ለመቀመጥ ችላለች፡፡

በጥቅሉ ሲታይ አዲሱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽንና አመራሮቹ ከለንደን መልስ ትልቅ ስራ የሚጠበቅባቸው እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

በተለይ ኳታር ከሁለት ዓት በኋላ ለምታስተናግደው 17ኛው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በውስን ርቀቶች ላይ ያለውን የኢትዮጵያን አትሌቲክስ በአይነትና በጥራት ማሳደግ አገሪቱ በዘርፉ ያላትን አቅም እንዲትጠቀም በር የሚከፍት ጥረት ይጠይቃል፡፡የለንደኑ ውጤትም ይህንኑ አሳይቶ አልፏል፡፡

ይሁንእንጂ በሚዳሊያ ሰንጠረዥ ላይ  ወርቅ ያስመዘገቡት አገራት ቁጥር 8 ብቻ ከመሆኑ አንፃር፣ ኢትዮጵያ ይዛው የተመለሰችው 2 ወርቅና ተጨማሪ 3 ብር ይበል የሚያሰኝና ለቀጣይ ተጨማሪ ስንቅ ሆኖ እንደሚያለግል ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡

መረጃ ጥንቅር፡‑ አዝመራው ሞሴ

/የመረጃ ምንጭ፡- የዓለም አትሌቲክስ ማህበርን /