በ89ኛው የኦስካር ሽልማት ላላ ላንድ በ6 ዘርፎች አሸናፊ ሆነ

የካቲት 20፡2009

በሆሊውድ በተካሄደው 89ኛው የኦስካር ሽልማት ላይ በ14 ዘርፎች የታጨው ላላ ላንድ የዓመቱ ምርት ሴት ተዋናኝ ዘርፍ ጨምሮ 6 ዘርፎች ኦስካር ለማሸነፍ ችሏል፡፡

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሩት ነጋ በታጨችበት ምርጥ የሴት ተዋናይ ኤማ ስቶን በላላ ላንድ ፊልም አሸናፊ መሆን ያቻለች ሲሆን የፊልሙ ዳይሬክተር ዴመን ቻዝል ምርጥ ዳይሬክተር ዘርፍን በ32 ዓመቱ ኦስካር ያሸነፈ በዕድሜ ትንሹ ዳይሬክተር ለመሆን ችሏል፡፡

ላላ ላንድ ፊልም ምርጥ ሲኒማቶግራፊ፣ ምርጥ ፕሮዳክሽን ዲዛይን፣ ምርጥ ስኮርና ምርጥ ወጥ የፊልም ሙዚቃ በሚሉ ዘርፎች ነው ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡

ሙን ላይት ፊልም ከአወዛጋቢ ስህተት በኋላ የአመቱ ምርጥ ምስል /ቤስት ፒክቸር/ አሸናፊ ሲሆን በፊልሙ ማኸርሻላ አሊ ምርጥ ወንድ ረዳት ተዋናኝ ዘርፍ ተሸልሟል፡፡

ፋይ ዱንዌ በመድረኩ ላይ የአመቱ ምርጥ ምስል አሸናፊ ሲያስተዋውቅ የተሰጠው ፅሁፍ ላይ ግን የአመቱን ምርጥ ሴት ተዋናይ ስም ኤማ ስቶን በላላ ላንድ የሚል ስለነበር ስህተቱ ተፈጥሯል፡፡ 

የላላ ላንድ ፊልም ቡድን በመድረኩ ላይ ሽልማታቸውን ተቀብለው ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በማመስገን ላይ በነበሩበት ወቅት ስህተቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ በአሳዛኝ ሁኔታ ሽልማቱን ለመመለስ ተገዷል፡፡

የዘንድሮውን 89ኛ የኦስካር ሽልማት መድረክ የመራው ጂሚ ኪሜል የተፈጠረውን ስህተት ከ2 ዓመታት በፊት ሚስ ዩኒቨርስ የቁንጅና ውድድር ላይ በስቲቭ ሃርቪ ከተፈጠረው ስህተት ጋር በማነፃፀር ታዳሚዎችን ፈገግ አሰኝቷል፡፡

ዴንዝል ዋሽንግተን በዋና ገፀ-ባህሪነት በተወነበትና ዳይሬክት ባደረገው ፌንስ የተሰኘ ፊልም ቪዮላ ዳቪስ ምርጥ ሴት ረዳት ተዋናይ ሽልማት ወስዳለች፡፡

ካሲ አፍሊክ ማንችስተር ባይ ዘ ሲ በሚለው ፊልሙ የዓመቱ ምርጥ ወንድ ተዋናይ ዘርፍ አሸናፊ ሲሆን ፊልሙ ምርጥ ወጥ ስክሪን ፕሌይ ለማሸነፍ ችሏል፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ እና ዘ ኒዮርክ ታይምስ