የ2009 ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 6 ምልከታዎች

በአዝመራው ሞሴ

እንደ መንደርደሪያ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2009 ዓ/ም ውድድር መርሃ ግብር በቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ውድድሩ እንደ አዲስ ከተጀመረ 1990 ዓ/ም ወዲህ ለ14ኛ ጊዜ ዋንጫውን አንስቷል፡፡

ይህም በአጠቃላይ የሊጉን ዋንጫ ያነሳበትን ቁጥር 29 አድርሷል፡፡ በዓመቱ የጨዋታዎች መቆራረጥ ተሽሎ የታየበት ቢሆንም ስፖርታዊ ጨዋነት አሁንም እግር ኳሱን በዳዴ ማስሄዱን ቀጥሏል፡፡

  1. የዓመቱ ትልቁ መነጋገሪያ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ትልቅ ስም እና ሀብት ያለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  እግር ኳስ ቡድን ወደ ከፍተኛ ሊጉ ወርዷል፡፡ ንግድ ባንክ በመጨረሻው ጨዋታ በሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ መረታቱ ወራጅነቱን አረጋግጧል፡፡ ንግድ ባንክ በፕሪሚየር ሊጉ ካለው የካበተ ልምድ እና  ጥሩ ስብስብ  አንጻር መውረዱ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡  የክለቡ የሀብት ምንጭ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም  ከብዙ ዓመታት በዓላ ስም አስጠሪውን እግር ኳስ ቡድን በሊጉ ውድድር አጥቷል፡፡

ሊጉ ከተጀመረበት 1990ዓ.ም አንስቶ ሁሉንም ዓመታት በተሳትፎ የዘለቀዉ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ወዳ ታችኛዉ ዲቪዚዮን ወርዷል፡፡

  1. መውጣት እና መውረድ

በቅርብ ዓመታት ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚያድጉ ክለቦች በአደጉ በዓመቱ መጨረሻ ተመልሰው መውረዳቸው እየተለመደ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ወልዲያ ከነማ  በመጣ በዓመቱ መመለሱ ይታወሳል፡፡ ከዚያም ከድክመቱ ወጥቶ ዳግም እራሱን አሳድጓል፡፡

በዚህ ዓመት ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ እና ጅማ አባቡና በመጡ ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊጉ ተመልሰዋል፡፡ በዉድድሩ ላይ ያለቸዉ ልምድ አነስተኛ መሆን፣ የተጨዋቾች ስብስብ እና በሀብት በቂ ዝግጅት አለማድርግ ደግሞ ግልጽ  ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በላይ ግን ከሜዳ ዉጭ ያሉትን የቤት ስራዎች አለመስራት ለክለቦች የቅርብ ጊዜ የመዉረድ ምክንያት ብቻ ሳይሆን ዉጤታማ ቡድኖች ዋንጫ አሳጥቷቸዋል፡፡ ጅማ አባቡና እና አዲስ አበባ ከተማ በዓመቱ ዋና አሰልጣኞቻቸዉን ከቀየሩት ክለቦች መካከል መሆናቸዉ የሚዘነጋ አይደለም፡፡

በተለይ አዲስ አበባ ከነማ በደካማ አቋም አስቀድሞ መውረዱን ያረጋገጠ ክለብ ሆኗል፡፡ ከሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የነበረው የነጥብ ልዩነትም 42 ነው፡፡

ጅማ አባቡና እስከመጨረው ጨዋታ በሊጉ የመቆየት ተስፋ የነበረው ቢሆንም በድሬዳዋ ተሸንፎ ከሊጉ አሳዛኝ ተሰናባች ሆኗል፡፡ ዉጤቱ በዚህ መልክ መሆኑ እንደ ድሬዳዋዉ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራዉ - ሞሪንሆ በብቃት የተገኘ ሲሆን፤ ለጅማ አባቡናዉ ገ/መድህን ኃይሌ ግን የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የዳኞች ምደባ እና የተዝረከረከ አሰራርን ለዉጤት ማጣታቸዉ እንደምክንያትነት አንስቷል፡፡ ይህ መውጣት እና መውረድ  የክለቦች በቂ የቤት ስራ ማነስ ይመስላል፡፡

የሊጉ አዲስ ክስተት

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ድምቀት በዋናነት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ሆነው ቆይተዋል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ የክልል ክለቦችም በደጋፊ ታጅበው የሊጉ ድምቀት መሆናቸውን ቀጥለዋል፡፡ ልክ እንደ አርባ ምንጭ እና ወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ሁሉ በዚህ ዓመት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች የሊጉ አዲስ ክስተት ሆነዋል፡፡ በዓመቱ በተለይ ፋሲል ከነማ ታላላቆችን ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊንን ማሸነፍ መቻሉ ለደጋፊዎች የበለጠ ወኔ እንደሰጠ ይታመናል፡፡

ሌላው የሊጉ አዲሱ ክስተት የወልድያ ስታዲዮም ነው፡፡ የወልድያ ስታዲዮም  ዓለም አቀፍ ደረጃውን ያሟላ የመጀመሪያው የሀገሪቱ ስታዲዮም መሆን ችሏል፡፡ የወልድያ እግር ኳስ ክለብም  በሊጉ ዘመናዊ ስታዲዮም ያለው ብቸኛው ክለብ ሆኗል፡፡

 

  1. አዲስ የግብ ክብረ ወሰን

ጌታነህ ከበደ ለ16 ዓመታት በዮርዳኖስ አባይ ተይዞ የቆየውን የግብ ክብረወሰን አሻሽሏል፡፡ ጌታነህ በዚህ ዓመት 25 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ነው ክብረ ወሰኑን ያሸሻለው፡፡

ዮርዳኖስ አባይ በ24 ግቦች ክብረ ወሰኑን ይዞ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ጌታነህ ከበደ በ2003 እና በ2005 የሊጉ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ መሆኑም ይታወሳል፡፡

  1. ቁጥሮች ምን አመላከቱ ስለ ሻምፒዮኑ

ባለፉት ሰባት ዓመታት ቅዱስ ጊዮርጊስ 5 ጊዜ የሊጉ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡  ደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና አሸናፊ በሆኑበት  2005 እና 2003 ዓ/ም ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ  ሁለተኛ ሆኖ ጨርሷል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2006 ዓ/ም የሊጉ ሻምፒዮን ሲሆን ተከታዩን ኢትዮጵያ ቡና በ20 ነጥብ ዋንጫ ያነሳበት ውጤት ባለፉት ሰባት ዓመታት ከፍተኛው ነው፡፡ በ2003 ዓ/ም የሊጉ መርሃ ግብር ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጦ ዋንጫውን አጥቷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ዓመት የሰበሰበው 62 ነጥብ በ2006 ዓ/ም ከሰበሰበው 68 ነጥብ ብቻ ያንሳል፡፡

  1. የዓመቱ አጨቃጫቂ ውሳኔ

በዓመቱ የተለያዩ ቅጣቶች በክለቦች፣ በተጨዋቾች እና አሰልጣኞች ላይ ተላልፈዋል፡፡ ትልቁ እና መነጋገሪያ ሆኖ የከረመው ውሳኔ ግን በሀዋሳ ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ላይ የተላለፈው የ1 ዓመት ቅጣት ውሳኔ ነው፡፡

አሰልጣኙ ድሬዳዋ ላይ በተደረገው ጨዋታ ያልተገባ ባህሪ አሳይተዋል በሚል ነው 1 ዓመት ከእግር ኳሱ  እንዲታገዱ እና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው፡፡ ይህም መነጋገሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ዘግይቶ በይገባኝ የአሰልጣኙ ቅጣት እንደተቀነሰ ሰምተናል፡፡

  1. ስፖርታዊ ጨዋነት

ስፖርታዊ ጨዋነት እንደዚህ ቀደሙ የእግር ኳስ ችግር ሆኖ በዚህ ዓመትም ቀጥሏል፡፡ የደጋፊዎች ዱላ ቀረሽ የድጋፍ አሰጣጥ እንዲሁም አልፎ አልፎ የታዩ ግጭቶች በዚህ ዓመትም ምነው እግር ኳሱ እንዲህ ከመርህ ወጣ የሚያስብል ሆኗል፡፡ ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች የዳኛን ውሳኔ ባለማክበር የፈጠሯቸው ግርግሮችም የገላጋይ ያለህ አስብሏል፡፡ የተዛባ የዳኞች ውሳኔ ለተለያዩ ግጭቶችም ምክንያት ሆነው ታይተዋል፡፡

ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ከመከላከያ ተጫውተው 4 ቀይ ካርድ የተመዘዘበት ጨዋታ ስፖርታዊ ጨዋነት የት እንዳለ ማሳያ ሊሆንም ይችላል፡፡

እንደማደማደሚያ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ለዘመናት የሚቆይ ታሪክ መፃፉን ቀጥሏል፡፡

እግር ኳሱም በቀጣይ ዓመታት ሰፊ ስራ እንደሚጠይቅ ዳግም አሳይቷል፡፡ ሰፖርታዊ ጨዋነት፣ የተዛባ ዳኝነት፣ የተጨዋቾቻችን እና አሰልጣኞቻችን  ስነ ምግባር አሁንም የእግር ኳሱ ችግር ሆነው የሚቀጥሉ ይመስላል፡፡ እነዚህ ችግሮች መጨረሻ እንዲኖራቸዉ ከተፈለገ ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ራሱን ከማሻሻል ጀምሮ ብዙ ለዉጦችን ሊያደርግ፣ አስተማሪ ዉሳኔዎችን ሊያሳልፍ፣ እግር ኳሱ የመቶ ሚሊዮኖች ኢንዱስትሪ መሆኑን ተገንዝቦ መስራት ያሻዋል፡፡ ፌደሬሽኑ ዉድድር እያካሄደ  (ያዉም ኋላ ቀር በሆነ አሰራር እየተመራ- የጨዋታ ሜዳዎች ከጨዋታዉ መጀመር ሰዓታት በፊት እየተፈለጉ፣ ዳኞች ከምደባ በኋላ በቂ ባልሆነ ምክንያት እየተቀየሩ፣ የሊጉ የዋንጫ ፉክክር ሳቢነት በማይታይበት፣ ሊጉ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንዲያገኝ እንኳ ፍላጎት በሌለበት . . .) ብቻ የኢትዮጵያን እግር ኳስ እቀይራለሁ ካለ ለዉጡ የማይታሰብ ነገር ያደርገዋል፡፡

ሊጉ ጅማ አባቡና፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እና አዲስ አበባ ከተማን አሰናብቶ አዲስ መጭ ክለቦችን በመጠበቅ ላይ ይገኛል፡፡ መጭ ክለቦችስ ለዚህ ለተንዛዛ ሊግ አዲስ ተስፋ ወይስ የባሰ ራስ ምታት ይሆኑ ይሆን አብረን የምናየዉ ይሆናል፡፡ ሊጉ ጥቅምት እንደሚጀመር ተስፋ በማድረግ እንሰነባበት፤ የዛ ሰው ይበለን!