ብሄር ብሄረሰቦች በአፋር ላይ ነግሰዋል

ህዳር 28፣2010

የ12ኛውን የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ለመዘገብ ወደ  አፋር ያቀናው የአቢሲ ሪፖርተር ዲባባ ቡራዩ ስለ በዓሉና ክልሉ ስላደረገው ዝግጅት እይታውን አጋርቶናል፡፡

የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት የጸደቀበት ህዳር 29 የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ተብሎ በአገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት እንዲከበር የተወሰነው ሚያዚያ 21 ቀን፣ 1998 ዓ.ም ነበር።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን እንዲከበርና በዋነኝነት የወሰነው የአገራችን ህዝቦች ፈቅደው ያጸደቁት ህገ-መንግስት ያስገኘላቸውን ጥቅሞች እንዲተገብሩትና ተጠቃሚነታቸውንም ለማረጋገጥ ታስቦ ነው።

የበዓሉ መከበር አገራችን የተያያዘችውን የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትግል አጠናክሮ  በማስቀጠል አገሪቱን ከድህነትና ከኋላቀርነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገውን ጥረት ለማፋጠን አንድነታቸውንና ህብረታቸውንም የሚያረጋግጡበት እንደሆነ ምክር ቤቱ በአፅንኦት ያምናል፡፡

የመጀመሪያው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በ1999 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር መከበር የጀመረ ሲሆን፣ እነሆ ዘንደሮ ደግሞ በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት ለ12ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡

እስካሁንም አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፤ የደቡብ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፤ የድሬደዋ አስተዳደርና አጎራባች ክልሎች (ኦሮሚያ፣አፋር፣ ኢትዮጵያ ሶማሌ፣ እና ሀረሪና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደር) ፤የትግራይ ክልላዊ መንግስት፤ የአማራ ክልላዊ መንግስት፤ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግስት፤የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት፣ የቤንሻንል ጉምዝ ክልላዊ መንግስት እና  የሃረሪ ክልላዊ መንግስት በየተራ ያዘጋጁ ሲሆን ዘንድሮም የአፋር ክልላዊ መንግስት አስተናጋጅነት ይከበራል፡፡

የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የብሄር፣ ብሄረሰቦችንና ህዝቦችን እኩልነት፣ አብሮ የመኖርና የመቻቻል እሴቶቻችንን ከማጎልበት ባሻገር ህዝቦች በአገራችን እየተመዘገበ ያለውን እድገት ለማስቀጠል ይህ ቀን ምቹ ሁኔታል ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል፡፡

በየክልሎቹ የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ሲከበር የበዓሉ ተሳታፊዎች የእያንዳንዱን ብሄር ባህልና ቋንቋ ያያሉ፤ ይማራሉ እንዲሁም ይደሰቱበታል፡፡ አዘጋጅ ከተማም በሺዎች የሚቆጠሩ የበዓሉ ተሳታፊችንና ተጋባዥ እንግዶችን ለማስተናገድ ሲባል የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ይካሄዳሉ፡፡

በበዓሉ ምክንያት የሚፈጠረው የቱሪዝም ገቢም እንዲሁ በተለይ በሆቴልና ግብይት ረገድ ለአካባቢው ህብረተሰብ ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታል፡፡

የበዓሉ አስተናጋጅ ከተማም ይህን በዓል ማስተናገድ መቻሉ የአገሪቱን እድገት በማዕከል ብቻ ሳይሆን በሁሉም አካባቢዎች ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው።

ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ገና ታዳጊ ቢሆንም  ስኬታማ የሆኑ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡

ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ሶማሌ፤ ሃረሪ፤ ቤኒሻምጉልና ጋምቤላ ክልሎች የብሄር ብሄረሰቦች ቀንን ያዘጋጁ ሲሆን የበዓሉ ተሳታፊዎችን ለማስተናገድ የተለያዩ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

የእንግዶች ማሪፊያዎች እንደ ሆቴል፤ የመዝናኛ ቦታዎችና ሊጎበኙ የሚችሉ ቅርሶችን በማሰናዳት የየራሳቸውን ባህልና ቅርስ አስጎብኝተዋል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ የበዓሉ ታዳሚዎች በቆይታቸው ወቅትም የተለያዩ ግብይትና ንግድ ስለሚያከናውኑ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ከፍተኛ ነበር፡፡

የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት 12ኛውን የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ህዳር 29 ፣2010 ያስተናግዳል፡፡ ለዚሁ ዝግጅት ይረዳ ዘንድም የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

እንደ ምሳሌ ተጠቃሽ የሚሆኑትም በርካታ የእንግዳ ማረፊዎች ግንባታ፤ በዓሉ የሚካሄድበት የክልሉ ስታዲዬም፤ መጋቢ መንገዶችን መገንባትና ጥገና ማድረግ፤ ትልቅ ዘመናዊ የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ ግንባታ፤ የቱሪስት መስህብ ቦታዎች እንዲጎበኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይገኝበታል፡፡

ከክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ባገኘነው መረጃ መሰረት እንግዶቹ እንዲጎበኙና የክልሉን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ በሰመራ ከተማ ባዛር ተዘጋጅቷል፡፡ ክልሉ የሰው ዘር መገኛ ስለመሆኑ የተረጋገጠበት የሉሲ ቅሪተ አካል መገኛ በመሆኑ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅበት የኤርታአሌ ገሞራና የጨው፤ የፖታሽና ሌሎች ማዕድናት በብዛት የሚገኝበት በመሆኑ ይህንን ሃብቱን ሌሎች ክልሎች ይበልጥ እንዲያውቁትና እንዲረዱት ለማድረግ ይሰራል፡፡

ከአሁን በፊት በነበሩት ስርዓቶች የክልሉ ህዝብ ከልማቱ ተጠቃሚ ሳይሆን ቀርቶ የበይ ተመልካች የነበረ፤ ማንነቱ ተዘንግቶ፤ ባህሉና ቋንቋውን እንዳይጠቀም የተደረገበት ጊዜ እንደነበር የበዓሉ አዘጋጆች ይገልፃሉ፡፡

ሀገሪቱ በምትከተለው የፌዴራሊዝም ስርዓት እና በህገ መንግስቱ በክልላዊ አስተዳደር  ተዋቅሮ ማንነቱን፤ ባህሉንና ቋንቋውን እንዲሁም እሴቱን መጠቀምና መንከባከብ መቻሉ ስርዓቱ የፈጠራው ቱርፋቶች መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡

ተጋባዥ እንግዶችም ይህንኑ ሃብቱን በመጎብኘትና በመገንዘብ የህዝቦችን አንድነት ማጠናከር፤ ሃገራዊ መግባባትን ለመፍጠር፤ ሌሎች ክልሎችም በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ይገልጻል፡፡

ታዲያ የክልሉ መንግስት ለብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክብረ በዓል መስተንግዶን ምክንያት በማድረግ ያከናወናቸው የልማት ስራዎች ወደ ፊትም ለህዝቡ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጡ ናቸው፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ ብሄር ብሄረሰቦች ተሰባስበው ከክልሉ ህዝቦች ጋር የሚያደርጉት የባህል፤ የቋንቋና እሴቶች ልውውጥ ክልሉ በሚገባ መልኩ ባህሉና ቋንቋው፤ የኢንቨስትመንት አማራጮቹ፤ የቱሪስት መስህቦቹ እንዲተዋወቅለት ይረዳል፡፡