ደቡብ አፍሪካዊቷ እንስት የሚስ ዩኒቨርስ የቁንጅና ውድድር አሸናፊ ሆነች

ህዳር 18፤2010

 የ22 አመቷ ደቡብ አፍሪካዊት ዴሚ ሌይግ ኔል በአሜሪካ ላስ ቬጋስ በተካሄደው የሚስ ዩኒቨርስ የዓለም የሴቶች ቁንጅና ውድድርን ማሸነፍ ችላለች፡፡

ዴሚ ሌይግ ኔል አሸናፊ መሆን የቻለችው ከዓለም ዙሪያ በተፎካካሪነት የቀረቡትን 92 እንስቶችን በመርታት ነው፡፡

ለዚህ ድል ያበቃት ደግሞ በኤችአይቪ ኤድስና በሴቶች እኩልነት ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደምትሰጥ በመናገሯ ነው ተብሏል፡፡

በተለይም ደግሞ ሴቶች ከወንዶች እኩል መስራት እየቻሉ እኩል ተከፋይ አለመሆናቸው እንደሚያበሳጫት ተናግራለች፡፡

በአንድ ወቅት በታጠቁ ሃይሎች ዘረፋ እንደተፈጸመባትና በዚህ ምክንያትም ሴቶች እራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችላቸውን ፕሮግራም ቀርጻ እየሰራች መሆኑንም ገልጻለች፡፡

ዴሚ ሌይግ ኔል የውድድሩ አሸናፊ በመሆኗ የአንድ ዓመት ሙሉ ደመወዝ፤ ቅንጡ አፓርታማ እና ሌሎች ከፍተኛ ሽልማቶችን አግኝታለች፡፡

ሴቶች ከተባበሩና አብረው የሚሰሩ ከሆነ ማንኛውንም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መከላከል ይችላሉ ብላለች፡፡

ዴሚ ሌይግ ኔል  የዚህ ውድድር አሸናፊ ስትሆን ሁለተኛዋ ደቡብ አፍሪካዊት ሴት እንደሆነች ተነግሯል፡፡

 ምንጭ፡ ታይም፤ ዘ ጋርዲያን