ኢትዮጵያዊቷ ተማሪ በሰብአዊነት የህግ መጣጥፍ ዓለም አቀፍ ውድድር ተሸላሚ ሆነች

ጥቅምት6 ፤2010

አለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት የህግ መጣጥፍ ውድድር አሸናፊ ለሆነችው ኢትዮጵያዊት ተማሪ እውቅናና ሽልማት ሰጥቷታል፡፡

በምስራቅ አፍሪካ የተዘጋጀውን የ2017 ውድድር ያሸነፈችው የመቀሌ ዩኒሸርስቲ ተማሪ ራሄል አለማየው አዲስ አበባ ከሚገኘው የአለማቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር ሽልማቷን ተቀብላለች፡፡

"The Application of International Humanitarian Law to Emerging Cyber Warfare" በሚል ርእስ በፃፈችው መጣጥፍ በምስራቅ አፍደሪካ ከሚገኙ 19 ዩኒቨርስቲዎች ከተውጣጡ የህግ ተማሪዎች ጋር በመወዳደር ነው ራሄል ለአሸናፊነት የበቃችው፡፡

ራሄል ከውድድሩ በፊት ስለዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህግ የነበራትን እውቀት ለማዳበር ከተለያዩ ምንጮች መረጃ ስታሰባስብና ስታነብ እንደነበር ገልፃለች፡፡

በዚህ ውድድር ኢትዮጵያዊ ተማሪ ሲያሸንፍ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን አለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን አስመልክቶ በህግ ተማሪዎች ዘንድ ያለው እውቀት እንዲጎለብት በማሰብ እንደዚህ አይነት ውድድሮችን በየአመቱ እንደሚያካሄድም ተገልጿል፡፡

ምንጭ፡ አለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር ኮሚቴ