የነፃትና የአንድነት ተምሳሌት - ዝክረ አድዋ በዓል

 

ዘመኑ 19ኛው ምዕተ ዓመት እየተገባደደ ያለበት ነው፡፡ አውሮፓዊያንና አሜሪካ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና በጦር መሳሪያ ሀይላቸው የፈረጠመበት የጊዜው ልዕለ ሀያል ሀገራት ነበሩ፡፡ በዚህም ጊዜ ሀገሮቹ በኢንዱስትሪ አብዮት ሂደት ውስጥ የነበሩበት ከመሆኑ ባለፈ በጥቁር ህዝቦች ላይ በጉልበት ያሻቸውን የሚያደጉበት ነፃነት የሚነፍጉበት ባሪያ የሚፈነግሉበት፣ በሀብትና ጉልበት የሚመዘብሩበት ጊዜም እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡

በወቅቱ ገናና የነበረው የጀርመኑ ቻንስለር ቢስማርክ 16 የአውሮፓ ዲፕሎማቶችን በጀርመን በርሊን እ.ኤ.አ 1884-1885 ሰበሰበ፡፡ የዘመኑ የቅኝ ግዛት አስፋፊ ሀያላን ሀገራት የአፍሪካ ካርታን ጠረጴዛችው ላይ አስቀምጠው በእጃቸው በያዙት ብዕር በማስመሪያ እያሰመሩ የአህጉሪቱን ሀብትና ሀይል እንዴት መመዝበር እንደሚችሉ በእብሪት መከሩ፡፡

ፋሺስት ጣሊያንም ተመሳሳይ ህልም በአፍሪካ ስለነበረው ግዛቱን ለማስፋፋት ወደ ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ አማተረ፡፡ በጊዜውም የአፄ ዮሐንስ ሞትን ተከትሎ  በአካባቢው ገዥዎች መካከል የስልጣን ሹኩቻ ተፈጥሯል፡፡ የወቅቱ የጣሊያን መንግስት ብልጣ ብልጥ በመሆን አልያም በጉልበት ሊገነባው የወጠነው ግዙፍ የቅኝ ግዛት ተልዕኮ ኢትዮጵያን ሳያምበረክክ እንደማያሳካ በማመኑ ሰላዮቹን የአማካሪ ለምድ አስለብሶ ወደ ኢትዮጵያ ማስገባቱን በአያሌ የታሪክ መዛግብት ተፅፏል፡፡ ከእነዚህም ሰላዮች መካከል የአፄ ምኒሊክ አማካሪ የነበረው ኮንታ አንቶኖሊ አንዱና ዋንኛው ነው፡፡

በጀርመን በርሊን አፍሪካን በቅኝ ግዛት ቀንበር በመቀራመቱ ሂደት የአውሮፓ ሀገራት ሲሳካላቸው ጣሊያን ግን በሴራው ዘግይታ ነበር የተሳተፈችው፡፡ ጣሊያንም ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛቷ ስር ለማዋል መንገድ የሚከፍትላትን የውጫሌ ስምምነት ከዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ጋር በውጫሌ ሜዳ በአምባሰል ተራራ እ.ኤ.አ ግንቦት 2፣1889 በተወካይዋ አንቶሌኒ ተፈራረመች፡፡ ስምምነቱም የውጫሌ ውል ተብሎ ይጠራል፡፡

ስምምነቱ ካካተታቸው 20 አንቀፆች ውስጥም በተለይ አንቀፅ 17 የአማርኛና የጣሊያንኛ ትርጓሜው ይለያያል፤ ለጦርነቱ መፈንዳትም ቀጥተኛ መንስኤ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የአንቀጹ አማርኛ ፍቺ ‹‹ግርማዊ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ከአውሮፓ መንግስት ጋር ግንኙነት ለማድረግ ወይም ለመነጋገር ሲፈልጉ በግርማዊ የጣሊያን ንጉስ አማካኝነት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡››የሚል ሲሆን የጣሊያንኛ ትርጉም ግን ‹‹የኢትዮጵያ መንግስት ከውጪ ሀገር መንግስታት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በጣሊያን መንግስት አማካኝነት ማድረግ ይገባዋል›› ይላል፡፡ የዚህ ፍቺ ኢትዮጵያ በጣሊያን ሞግዚት አስተዳደር ስር መሆኗን የሚገልጽ ነው፡፡ይህንንም የጣሊያን መንግስት ለአውሮፓ መንግስታት በደብዳቤ አሳወቀ፤ ኢትዮጵያም በእኔ ስር ነች በማለት እወቁልኝ አለ፡፡

በእሾህ የተለወሰው አንቀጽ 17 የትርጉም ስህተት እንደነበረው ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ለማወቅ ቻሉ፡፡ ውሉንም አለመቀበላቸውን በይፋ ለአውሮፓ ሀያላን ሀገራት ከመግለፃቸው በፊት ውሉ እንዲስተካከል ለጣሊያን መንግስት በተደጋጋሚ ደብዳቤ ቢጽፎም ምላሹ የውሃ ሽታ ሆነ፡፡ ጉዳዮን በሰላም ለመፍታት የበርካታ ሀገራትን ሽምግልና ቢጠይቁም ይህም ሳይሳካ ቀረ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የውጫሌ ስምምነትን እንደማይቀበለው ኮንት አንቶሌኒ ሲያውቅ አፄ ምኒሊክ እልፍኝ ገብቶ ደነፋ፡፡ የጣሊያን መንግስት ይህን እንደውርደት ስለሚቆጥረው ክብሩን በጉልበት ያስጠብቃል ብሎ ፎከረ፡፡

የአፄ ምኒሊክ ባለቤት እቴጌ ጣይቱ ከብዙ በጥቂቱ ለአንቶሌኒ እንዲህ አሉት ‹‹የዛሬ ሳምንት አድርገው፡፡ እኔ ሴት ነኝ፡፡ ጦርነት አልወድም ነገር ግን ሀገሬን እንደዚህ ያለ ክብር የሚነካ ዘለፋ ከምትሸከም ጦርነትን እመርጣለሁ፡፡ ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ! እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር አስጥቶ ደሙን ለሀገሩ ፍቅር አፍስሶ ለአፈሩ ክብር ለብሶ እሱ ወድቆ ሀገሩን የማያቆም እዚህ ያለ እንዳይመስልህ! ሂድ! የኢትዮጵያን ሰው ባታውቀው ነው፡፡››

የጣሊያን መንግስት በተወካዩ አማካኝነት ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ሲያውጅ አፄ ምኒሊክ ጣሊያን በጦር መሳሪያም ሆነ በስልጣኔ ከፍ ማለቱ ሳያሸብራቸው ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት በማለት አዋጅ አስነገሩ ፡፡ ‹‹የሀገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም አንተም አላስቀየምከኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፤ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ለሚስትህ ለሃይማኖትህ ስትል በፀሎትህ እርዳኝ፡፡ ወስልትህ የቀረህ ግን ሃላ ትጣላኛለህ አልተውህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዮ በጥቅምት ነው እና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ፡፡›› ማለታቸውን ታዋቂው ጋዜጠኛና ፀሐፊ ጳውሎስ ኞኞ አፄ ምኒሊክ በሚለው መጸሐፉ አስፍሯል፡፡

አዋጁን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጠላትን ለመፋለም ከዳር እስከ ዳር በባዶ እግራቸው ተመሙ፡፡ የወቅቱ የጣሊያን መንግስትም ቀደም ብሎ በመቐሌና በአምባላጌ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰራዊቱን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ አስታጥቆ  በአድዋ ተራሮች ስር ሲከትም በባህላዊ መሳሪያ የታጠቀው የኢትዮጵያ ጦር ወደ አድዋ ለአምስት ወራት ገስግሶ ጦርነቱን ይጠባበቅ ጀመር፡፡

የካቲት 23፣ 1888 ዓ.ም ወይም (እ አ አ ማርች 1፣1896) ጀምበር ሳትገልጥ የማይቀረው ጦርነት ፈነዳ፡፡ ከንጋቱ 12 ሰዓት አካባቢ እንዳየሱስ በተባለ ቦታ ኢትዮጵያዊያኑ  በጠላት ላይ ጥቃት ፈፀሙ፡፡ በዚህ ጊዜ የጣሊያን ጦር መሪ አልበርቶኒ የሌሎች አጋር ጀነራሎችን እርዳታ ጠየቀ፡፡ የጀነራል ዳቦርሜዳ ብርጌድ ጥያቄውን ተከትሎ ለእርዳታ ቢንቀሳቀስም በኢትዮጵያዊያን ተይዞ አከርካሪው ተመታ፡፡ ሽንፈቱን ከማለዳው የተረዳው የኤርትራ ምክትል ገዥ  ላምቤርቶ ወደ ጣሊያን ሮም መልዕክት መላኩን አፄ ምኒሊክ በሚለው መጸሐፍ ተጠቅሷል፡፡

ጦርነቱም በግማሽ ቀን በጀግኖች አባቶቻችን ድል ተደመደመ፡፡ የወቅቱ ወራሪ ሀይል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮቹ ከፊሉ ሲገደሉ ገሚሱ ደግሞ ተማረኩ፡፡ ቀሪዎቹም እራሳቸውን ለማትረፍ ፈረጠጡ፡፡

የአድዋ ድል አንፀባራቂ ቱሩፋቶች

ዘመን ተሻጋሪው የአድዋ የድል የጥንቶቹ አባቶቻችን ጀግንነትና ሀገር ፍቅር የተመሰከረበትና የቅኝ ገዥዎችን እብጠት ያስተነፈሰ፤ የኢትዮጵያዊያንን ነፃነት አንድነትና የሀገር ሉዓላዊነት ያስከበረ፤ በጭቆና ለሚማቅቁ ጥቁሮች የነፃነት ማቀጣጠያ ክብሪት የሆነ፤ ለፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሰረት የጣለ ታላቅ ገድል መሆኑን አያሌ ፀሐፍት በድርሳናቸው ጠቅሰዋል፡፡

የአድዋ ድል ኢትዮጵያን በሰፊው ያስተዋወቀ የታሪክ ክስተት ነው፡፡ በወቅቱ የነበሩት የአሜሪካና የአውሮፓ ጋዜጦችና መጽሔቶች አቋማቸውን በመቀየር ድሉ ታላቅ ገድል መሆኑንና አፄ ምኒሊክም ታላቅ መሪ እንደነበሩ መስክረዋል፡፡

የአድዋ ድል ከኢትዮጵያዊያን አልፎ ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ መኩሪያ መመኪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ጥቁሮች ለነፃነታቸው ያደርጉ የነበሩት ትግል አድዋን መሰረትና መነሻ በማድረግ ነበር፡፡ በዚህም ድሉ ነፃነታቸውን ለማረጋገጥ መነሳሳትን ፈጥሮላቸዋል፡፡ ጥቁር ለዓላማው መሳካት በአንድነት ከታገለ ጠላትን ማሸነፍ እንደሚችል ድሉ ጽኑ እምነት እንዲይዙ አድርጓል፡፡ በዚህም አውሮፓዊያን ትምህርት ያገኙበት በመሆኑ ወራሪ ቅኝ ገዥዎች የአገዛዝ ፖሊሲያቸውን ጭምር እንዲመረምሩ አድርጓል፡፡

ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባሳተመው በራሪ ወረቀት ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ የአድዋ ተራሮች ዙሪያ በአራት ብርጌድ የተከፈለ ሃያ ሺህ ዘመናዊ ጦር ያሰለፈው የጣሊያን ጦር በአብዛኛው ጦርና ጋሻ ከያዘ መቶ ሺህ የሚጠጋ የኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር ተዋግቶ በጥቂት ሰዓታት የተሸነፈበት አዲስ ታሪክ ነው ይለናል፡፡ በጥቂት ሰዓታት የኢትዮጵያዊያን የጀግንነት ትግል ሰባት ሺህ ኢጣሊያዊያን ሞተው፣ ሁለት ሺህ ቆስለው፣ ሶሶት ሺህ ተማርከው፣ ሸሽተው ያመለጡ ወታደሮች ቢኖሩም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የጣሊያን የጦር መሣሪያ በኢትዮጵያዊያን የተማረከበት ልዩ የታሪክ ክስተት ነው፡፡

በዚህም የአድዋ ድል በነጮችና በኢምፔሪያሊዝም ላይ የተገኘ የመጀመሪያው የጥቁር ህዝቦች ግዙፍ ድል ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ ነፃነት በአዲስ ውል በይፋ በማረጋገጥም የቅኝ ግዛት መስፋፋትና ውድቀት አይቀሬነት ታወጀ፡፡ ኢትዮጵያም በዓለም መድረኮች ላይ የክብር ካባን ተጎናፀፈች፤ ተፅዕኖ ፈጣሪነቷ የዓለም ሀገራትን ቀልብ ሳበ፤

በሁለት ዓመት ውስጥ ሶስቱ የምስራቅ አፍሪካ  ቅኝ ገዥ ሀገራት እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ድንበራቸውን ለማካለል ስምምነት ፈረሙ፡፡ ሀገራችንም በቅኝ ግዛት ዘመን ከቅኝ ገዢዎች ጋር ተደራድራ ድንበሯን በማስከበር ልዩ ታሪክ ፅፈች፡፡

ይህን ተከትሎም የጊዜው የዓለም ኃያላን ሀገራት ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ቱርክ፣ ቤልጂየም፣ ተሸናፊዋ ጣሊያንና አሜሪካ ኤምባሲያቸውን በትንሿና አዲሷ መዲና በአዲስ አበባ በመክፈት ዲኘሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር ተሽቀዳደሙ፡፡ የንግድ ግንኙነት ለመጀመርም መፎካከር ያዙ፡፡ በዓለም ላይ መታየት የጀመረ የአውሮፓውያን የስልጣኔ ውጤቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ተሽቀዳደሙ፡፡ ከድሉ በኋላ አንድ ዓመት ሳይሞላ ፈረንሳይ የኢትዮ-ጁቡቲ የባቡር መስመር ለመዘርጋት ውል ገባች፤ ይህ የኢትዮጵያዊያን የተወከለ የጥቁር ህዝቦች ድል አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውጤቱም ሰፊ ሆነ፡፡ ምዕራባዊያን ለመቶ ዓመታት በጥቁርና ሌሎች ጭቁን ህዝቦች ላይ የገነቡት የበላይነት አስተሳሰብ ተሸነፈ፡፡ በአውሮፓውያኑ ወረራ ተሸማቀው የነበሩ አፍሪካዊያንና የካሪቢያን ህዝቦች ተስፋና ክብር አገኙ፡፡ ድሉም የተጫነባቸው የበታችነት መንፈስ ላይ እንዲያምፁ በር ከፈተላቸው፡፡

ጥቁር አሜሪካዊያን፣ የካሪቢያን ህዝቦችና ምሁሮቻቸው በአድዋው ድል ምክንያት የመነቃቃት መንፈስ አገኙ፣ በዚህም ለፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ መመስረትም ምክንያት ሆነ፡፡ ቆይቶም አፍሪካዊያን ስለአንድነታቸው ሲመክሩ አዲስ አበባን ዋና መዲናቸው በማድረግ ለአድዋ ድል ዕውቅናን ሰጡ፡፡

ለአድዋ ድል ምክንያት የሆኑ አንድ መቶ ሺህ ተዋጊዎችና የጦርነቱ መሪዎች፣ አንድ መቶ ሺህ ስንቅ ያልያዘ ጦር ለወራት ግብር እያዋሉ የመገቡ እናቶች፣ ለዚህ ሁሉ ሰራዊት የዕለት ቀለብ እያሰባሰበ ያቀረበ አርሶ አደር ሁሉ የድሉ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ከጦሩ ጀርባ የተሰራውን ምግብ በእንቅብ ተሸክመው ይውሉ የነበሩ ጎበዛዝት፣ ከመቶ ሺህ ጦር ጀርባ ቁስለኛ እያነሱ ያርቁና ያክሙ የነበሩ ጠቢባን፣ ለዛ ሁሉ ሰራዊት የሚሆን ስንቅና ትጥቅ የጫኑ እንሰሳትን የሚንከባከቡ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የድሉ ባለቤቶች ናቸው፡፡ የድሉን መንፈስ ለነፃነታቸው አርማ ያደረጉ ጥቁር ህዝቦች፣ በወቅቱ ድሉን ለዓለም ጭቁን ህዝቦች ያስተዋወቁ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና የጥቁሮች መብት ታጋዮች ሁሉ የአድዋ ድል ባለቤቶች ናቸው፡፡

የአድዋ ድልን ተከትሎ ኃያላን ሀገራት ለወዳጅነት የፈለጉንን ያህል አሁንም ብዙዎች ከኛ ጋር ለመስራት የሚመርጧት ሀገር እየፈጠርን ነው፡፡ በዚህም አዲስ አበባ ከዓለም ጥቂት የዲኘሎማቲክ ከተሞች መካከል ዋናዋ ሆናለች፡፡

የአድዋ ድል ነፃነታችንን እንዳስከበረ ሁሉ አሁንም የፖሊሲ ነፃነታችንን በላቀ፣ አስተማማኝና ሥር ነቀል በሆነ መልኩ ማስከበር ችለናል፡፡

የአድዋ ድል የወቅቱን የስልጣኔ ውጤቶች እንድንጠቀም /ባቡር፣ ስልክ፣ መኪና/ በር እንደከፈተልን ሁሉ አሁንም በራሳችን አቅም ጭምር ተዓምር የሚባሉ ኘሮጀክቶች ሰርተን የማጠናቀቅ አቅም ፈጥረናል፡፡ አሁን እየተዘረጉ ያሉ ባቡሮች ከመቶ ዓመት በፊት ከአድዋ ድል በኋላ ጅምሩን አይተን የቆመው ልማት በላቀ ደረጃ የቀጠለበት ነው፡፡

የአድዋ ድል የሉዓላዊነታችን መከበር ምልክት የሆኑ ድንበሮቻችንን ከወቅቱ ጉልበተኞች ጋር ያካለልንበት እንደሆነ ሁሉ አሁንም ለመቶ ዓመታት ያስፈራሩንን አካላት አሸንፈን በአባይ ወንዝ ላይ የመጨረሻውን ግዙፉን ግድብ በራሳችን አቅም መስራት ያስቻለን ነው፡፡

የአድዋ ድል ለፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ማበብ ምክንያት እንደሆነ ሁሉ አሁንም ኔፓድን በመሠሉ መርኃ ግብሮች አፍሪካን ከድህነት ለማውጣት፣ የራሷን ጉዳይ በራሷ እንድትፈታ ለማስቻል የሀገራችን ሚና የማይተካና ግንባር ቀደም እየሆነ ነው፡፡

ስለሆነም የአድዋ ዘመን ትውልድና አሁን ያለው ትውልድ በሁለት ክ/ዘመኖች ውስጥ፣ በሀገራችን የተመዘገቡ የሁለት ግዙፍ ድሎች ባለቤት ናቸው፡፡ የሁለቱም ድሎች ምክንያት ደግሞ የህዝቦች ለሀገራቸው ሉዓላዊ ክብር ግንባር ቀደም ባለቤት መሆናቸው ነው፡፡

በአጠቃላይ ያለፈው ትውልድ የነበረው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዴሞክራሲያዊ ችግሮች ውስጥ ሆኖ የነበረችውን ውስን ነፃነት ተስፋ በማድረግ ሀገሩን በአንድነት ተከላክሏል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ያኔ የነበረውን ጉድለት የሞላ፣ የነበረውን የሀገር ክብር በጋራ የመቆም እሴት በዘላቂ መሠረት ላይ ለማቆም እየታተረ የሚገኝ ነው፡፡ በዚህም ጥረቱም በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የመቶ ዓመታት ድህነትን መሸርሸር ጀምሯል ሲል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባሳተመው ጽሁፉ ያትታል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጀግኖች አባቶቻችን ህይወታቸውን ገብረው ጦርነቱን በድል የተወጡበትን 121ኛ የአድዋ የድል በዓል ‹‹የአድዋ ድል ብዝሃነትን ላከበረች ኢትዮጵያ ድህነትን ለማሻነፍ የሚያስችል ህያው አብነት›› በሚል መሪ ቃል በመላ በሀገሪቱ በድምቀት ያከብራሉ፡፡

ጥንቅር በሰለሞን አብርሃ